Logo
EBC
ምፅዓተ ጂኦ-ፖለቲካ እና የባሕር በር አጀንዳችን
****************

ዓለማችን ከአንድ ዋልታ ወደ ብዝኃ-ዓለማዊ ሥርዓት የኃይል ሽግግር እያደረገች ባለችበት በአሁኑ ዘመን፣ የጂኦ-ፖለቲካው ዐውሎ ነፋስ በድጋሚ እያንሰራራ ይገኛል።

ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ ተቀዛቅዞ የነበረው የኃያላን ሀገራት የእርስ በርስ የጂኦ-ፖለቲካዊ ሽኩቻ በማገርሸቱ፣ የቀይ ባሕር እና የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ዳግም የዓለም አቀፍ ትኩረት ማዕከል ሆኗል።

ሀገራት ጥቅማቸውን ለማስከበር እና የዓለም መሪ ለመሆን በሚያደርጉት ፉክክር፣ የዓለም ኃይል እና ሀብት የተከማቸባቸውን ቦታዎች ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥድፊያ "ምፅዓተ ጂኦ-ፖለቲካን" በይፋ አውጇል።

በአሁኑ ወቅት የኃያላኑ ግብግብ በተለይም የንግድ መስመሮችን እና ስትራቴጂያዊ የባሕር ሰርጦችን መቆጣጠር ላይ ያነጣጠረ ነው።

በታሪክ የምድርን ማዕከላዊ መሬት እና የባሕር ዳርቻን መቆጣጠር ዓለምን መቆጣጠር ነው የሚሉት የሀልፎርድ ማኪንደር እና የኒኮላስ ስፓይክማን ክላሲካል ፅንሰ-ሐሳቦች በድጋሚ የዓለም መድረክ ላይ ተግባራዊ እየሆኑ ይገኛሉ።

በዚህ ፉክክር መካከል ቀይ ባሕር፥ አፍሪካን፣ አውሮፓን እና እስያን የሚያገናኝ ድልድይ በመሆኑ የጂኦ-ፖለቲካ ፉክክር ማዕከል ሆኗል።

በዚህ ውስብስብ የጂኦ-ፖለቲካ ፍጥጫ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ምሰሶነት ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው። ትልቅ የሕዝብ ቁጥር ያላት እና በነፃነት ታሪኳ የምትታወቀው ኢትዮጵያ፣ በቀጣናው ፖለቲካ የላቀ አቅም ያላት ዋልታ ናት።

ይሁን እንጂ 97 በመቶ የሚጠጋ ምርቷን ለማስገባት በአንድ ሀገር ላይ ብቻ ጥገኛ መሆኗ፣ ሀገራችን በስትራቴጂያዊ የባሕር በር እጦት እንድትፈተን አድርጓታል።

ስለሆነም፣ ኢትዮጵያ ከታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ገናንነቷ አኳያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘት የግድ ይላታል።

ስንት ሺሕ ኪሎሜትር አቋርጠው የመጡ የውጭ ኃይሎች አፍንጫችን ሥር ወታደራዊ የጦር ሰፈር በገነቡበት በዚህ ዘመን፣ ቀጣናዊ ዋልታ የሆነችው ሀገራችን የራሷን የባሕር ኃይል እና ወታደራዊ ቤዝ ለማደራጀት መመኘቷ ሉዓላዊ መብት ከመሆኑም ባሻገር ለቀጣናው ሰላም እና አንድነት መጠበቅ ወሳኝ እርምጃ ነው።

ከዚህ ሁሉ አዙሪት እና የኃያላን የእጅ አዙር ጦርነት ለመውጣት የሚያስችለው ስትራቴጂያዊ መንገድ "መደመር" ነው። ኢትዮጵያ ያላት ሰፊ ገበያ እና የውኃ ሀብት፣ የጎረቤት ሀገራት ካላቸው የባሕር በር ጋር ተቀናጅቶ አካባቢውን በጋራ የማልማት ትልቅ አቅም አለው።

የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በታሪክ፣ በባህል እና በሃይማኖት የተሣሠሩ ወንድማማች ሕዝቦች በመሆናቸው፣ አብሮነታቸውን ድንበር ሊገድበው አይገባም።

ጥላቻን አስወግዶ፣ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ትሥሥር በመፍጠር፣ ወሰን ተሻጋሪ የንግድ ግንኙነትን ማጠናከር የውዴታ ግዴታ ነው።

የቀጣናው ሀገራት እርስ በርስ ከመጋጨት ይልቅ ቢተባበሩ እና የሌሎችን ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በመረዳት ቢደጋገፉ፣ ቀጣናውን ከግጭት የፀዳ በማድረግ ወደ ላቀ ብልጽግና ማሸጋገር ይችላሉ።

የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅም የሚረጋገጠውም ሆነ የቀጣናው ዕጣ ፈንታ ብሩህ የሚሆነው ይህ የትብብር እና የመደመር መንፈስ በተግባር ሲመነዘር ብቻ ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
#ebc #ethiopia #medemer #redsea #nationalinterest

14 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.