Logo
FBC
ሰላም፤ እንደምን አደራችሁ?

ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያችን የክተት አዋጅ አወጀች፡፡
እንኳንስ እናት ሀገር ጠርታ፤ ለሩዋንዳ የደረሱት፣ ሞቃዲሾን የታደጉት፣ የኮሪያ ጀብደኞች፣ የቡሩንዲ ሰላምተኛ፣ የዳርፉር የፀጥታ ዘቦች የሆኑት የቁርጥ ቀን ልጆቿ ሆ… ብለው ተነሱ፡፡

ለሳልሳዊት ዓድዋ ልጆቿ በፍፁም አንድነትና የመንፈስ ከፍታ በአራቱም ማዕዘን ተመሙ፡፡

ስንቃቸው ፅናት፣ ትጥቃቸው አካፋና ዶማ፣ ርዕያቸው ደግሞ የልጅ ልጆቻቸውን ሀገር መስራት ነበር፡፡

እናማ ወርሀ ሐምሌ በ22ኛው ዕለት 2011 ዓ.ም ኢትዮጵያዊያን ሜዳውን አቋርጠው፣ ጋራውን እየቧጠጡ፣ ሸንተረሩን ይኩሉት፥ ሸለቆውን ሸማ ያለብሱት ያዙ፡፡

በ12 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ድል በድል ሆኑ፡፡

ዜጎች በመሪያቸው ሐሳብ አፍላቂነት እና ጥሪ እልፍ ሆነው አንደ አንድ፤ አንድ ሆነው እንደ ሺህ ታላቁን ታሪክ ሰሩ፡፡

በአንድ ጀምበር ከ350 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል የዓለምን ማህበረሰብ አስደመሙ።

ከአያት ቅድመ አያታቸው የወረሱትን የጦር ሜዳ ጀግንነት፣ ጥበብ እና የድል አድራጊነት መንፈስ ተፈጥሮን በመታደግ ደገሙ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የገዘፈ ሐሳብ እስካሁን 48 ቢሊየን ችግኞችን ተክሎ፤ ዘንድሮ ለ8 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ተከላ ተዘጋጅቷል፡፡

ይህ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የዓለምን ትኩረት የሳበው መርሐ ግብር በታላላቅ የሀገር እና የተቋማት መሪዎች ተዓምራዊ የተባለለት ነበር፡፡

ከእነዚህ መካከል፡-

 የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን፣

"ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰተውን ድርቅና የአፈር መሸርሸር ለመቋቋም የያዘችው ስትራቴጂ ፍጹም ውጤታማ ነው፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ማበረታቻ ነው፡፡"

 የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

"ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚያደርገው ትግል ውስጥ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ አማካኝነት እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት በተግባር የተደገፈ መሪነት (Practical Leadership) ምን ማለት እንደሆነ ያሳያል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዛፎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መትከል ትልቅ የተስፋ መልዕክት ነው።"

 የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን

"የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ እጅግ አስደናቂ እና መላው ዓለም ሊከተለው የሚገባ ትልቅ አርአያ ነው። የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ቃል ከመግባት ባለፈ በተግባር ማሳየት እንደሚቻል ኢትዮጵያ ለዓለም እያሳየች ነው። ይህ ለወደፊቱ ትውልድ የሚተርፍ ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው።"

 የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ

"የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ በአህጉራችን አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለምናደርገው ጥረት ትልቅ ማስተማሪያና ማበረታቻ ነው።

ኢትዮጵያ በተግባር ያሳየችው ቁርጠኝነት እኛም በኬንያ ተመሳሳይ ታላቅ ግብ እንድንሰንቅ አድርጎናል" በማለት ተናግረዋል።

ሌሎች መሪዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከክስተት በላይ ስለመሆኑ በአድናቆት ተናግረዋል፤ ጽፈዋል፡፡

ጉዳዩ ወዲህ ነው ይህን ከእሳቤ መሬት የነካ፡ ብሎም እንደ ዐውድ ዓመት የሚናፈቅ እንደ ባሕል የሚደመቅበትን የአረንጓዴ ልማት ተግባር ዘንድሮ ለመድገም ምን ያህል ተዘጋጅተናል የሚለው ነው?

ጉዞ ወደ የልጅ ልጆቻችን ሀገር ኢትዮጵያ! ዳግም ድል 8 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል በመዘጋጀት፣ በመትከል እና በመንከባከብ፡፡

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.