Logo
FBC
በዘመናት መካከል የጸኑ ደጋፊዎች የደስታ ምሽት...

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) "አርሰናል ዋንጫ ይበላል?" አዎ ሆኗል መልሱ። የለንደን ሰማይ ወደ ቀይነት ተቀይሯል። የመድፈኞቹ ትንሳኤ ከ22 አመት በኋላ በቬታሊቲ ስታዲየም ተበስሯል ።

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ (ከፈረንጆቹ 2004 ጀምሮ) የዘለቀው የአርሰናል ደጋፊዎች የዋንጫ ጥማት ሊሽር የአንዲት ነፍስ ወደ ምድር መጥታ ወጣት እስክትባል ተስፋ አስቆራጭ ነበር ።

ደጋፊዎቹ ግን በፅናት ስንት ጉድ መጥቶ በሄደበት ትንፋሻቸውን ውጠው ጠብቀዋል።

ዓለም ቅርጿን ብትቀያይር የአለም ዋንጫ ወደ አፍሪካ ምድር ቢመጣ፣ እነ ቤጂንግ የሉሏ ዘዋሪ ቢሆኑ፣ ኢትዮጵያ ዓባይን ገድባ ድግሷን ብትመርቅም አርሰናል ግን ዋንጫ አልበላም።

ዛሬ ግን ኤሚሬትስ ስታዲየም የናፈቀውን የፕሪሚየር ሊግ ክብር ዳግም አጊንቶ የደጋፊዎቹ ምድር ርዳለች ። ምድር አርግዳለች ።

ዋንጫው አርሰናል ዛሬ ላይ በቆመበት ደረጃ በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን፣ ባለፉት አራት ዓመታት ሚኬል አርቴታ በትዕግስት የገነባው ሂደትን የማመን ፍሬ ነው።

ታዋቂው የእግር ኳስ ተንታኝ ጂሚ ካራገር በቅርቡ በሰጠው ትንታኔ፣ "የዘንድሮው አርሰናል ካለፉት ሁለት ዓመታት የሚለየው በአእምሮ ጥንካሬው ነው" ብሎ ነበር።

መድፈኞቹ ቀደም ሲል ወሳኝ ጨዋታዎች ላይ የመንሸራተት ባህሪ ነበራቸው፤ ዘንድሮ ግን በሜዳቸውም ሆነ ከሜዳቸው ውጪ እንደ ሻምፒዮን መጫወትን ተላምደዋል።

በመከላከሉ ረገድ የገነቡት የብረት ግንብ ለሊጉ ጥቂት ጎል ተቆጣሪ ቡድን እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

በመካከለኛው ክፍል ደግሞ እንግሊዛዊው ዴክላን ራይስ የቡድኑ ሞተር በመሆን መከላከሉንና ማጥቃቱን በሚገርም ሁኔታ አስተሳስሮታል።

"እግር ኳስ በሜዳ ላይ ቢጫወትም አሸናፊው ግን በቁጥሮች ውስጥ ቀድሞ ይታያል" እንደሚባለው ሁሉ፣ የመረጃ ትንታኔዎች ለአርሰናል ትልቅ ተስፋ ነበራቸው።

አርሰናል ዘንድሮ በንፁህ ግብ መውጣት የሊጉን ክብረ ወሰን አድሷል ፤ ግብ ጠባቂው የወርቅ ዋንጫን ወስዷል።

እንግሊዛዊው ተንታኝ ጋሪ ኔቭል "አርሰናል ዘንድሮ ያንን የድል ተራራ መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ተራራው ላይ ባንዲራቸውን ለመትከል የሚያስችል ትጥቅ እንዳላቸው አሳይተዋል።"

ተንታኞች እንደሚስማሙት አርሰናል ካለፈው ዓመት ስህተቱ ተምሮ ስብስቡን በማስፋቱ፣ ተጫዋቾች ቢደክሙም የሚተኩት አቅም ተመሳሳይ ሆኗል።

የሊጉ ዋንጫ እጣ ፈንታ በሁለት ስፔናውያን አሰልጣኞች ፍልሚያ ሆኖ ፔፕ ጋርዲዮላን ለስንብት አርቴታን ለአሸናፊነት አብቅቷል።

ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ እንደሚባለው አርቴታ በጭንቅም ቢሆን የናፈቀውን ዋንጫ ለመሳም ታድሏል።

የ "ኖርዝ ለንደን ፎርኤቨር" መዝሙር በኤምሬትስ ሰማይ ስር በድል አድራጊነት እየተዘመረ ነው ።

የሉዊስ ደንፎርድ ግጥሞች "ይህ የደሜ ቀለም ነው፤ ለዘላለም የኔ ነው" እያሉ ሲያስተጋቡ፣ በደጋፊዎች አይን ላይ የሚታየው እንባ የክለቡን ጥልቅ ትስስር ያሳያል።

ይህ መዝሙር ደጋፊውን ከመጫወቻ ሜዳው ጋር በማስተሳሰር፣ ተጫዋቾቹ እስከ መጨረሻው ሰከንድ እንዲዋጉ የሚያደርግ የሞራል ስንቅ ነበር ።

ደጋፊዎቹ ቀይ ጭስ በማዘጋጀት ለንደንን ወደ ቀይ ቀለም ለመቀየር ቆርጠዋል። ይህ ድል ለደጋፊዎቹ ከእግር ኳስ ዋንጫ በላይ ነው፤ የለንደን የበላይነትን ዳግም የሚያረጋግጡበት ታላቅ ክስተት ነው።

አርሰናል ዋንጫ ይበላል? አዎ! የተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተመልካች ዓለም ነዋሪዎች የሚቀበሉት እውነት ሆኗል።

የመድፈኞቹ የቀረረው እንባ በደስታ ፈንጠዝያ ባሉበት የምድር ጫፍ ተተክቷል።

በኃይለኢየሱስ መኮንን

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.