Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ታዋቂው ምሁር፣ አንጋፋው የፖለቲካ መሪ እና የማህበራዊ ፍትህ ተሟጋች የነበሩትን የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን የህይወት ዘመን አበርክቶ ለመዘከር እና ውርሳቸውን በበጎ ተግባር ለማስቀጠል ያለመ ልዩ የህዝብ መሰብሰቢያ መርሃ ግብር በሲያትል ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት መዘጋጀቱን የፕሮፌሰሩ ቤተሰቦች ለዘ-ሐበሻ አስታወቁ ። ይህ መድረክ የቀድሞውን ምሁር ስራዎች ከማሰብ ባሻገር፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍን ለማሳደግ ታስቦ በተቋቋመው "የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ፋውንዴሽን" ዙሪያ ሰፊ ውይይት ለማድረግ እና ድጋፍ ለማሰባሰብ የተዘጋጀ ነው።

መምጣት የሚፈልጉ የማህበረሰቡ አባላት ቅዳሜ ግንቦት 15 ቀን 2018 ዓ.ም (ማለትም እ.ኤ.አ. ሜይ 23 ቀን 2026) ከሰዓት በኋላ ከ8 ሰዓት ከ30 እስከ 11 ሰዓት ከ30 (በሲያትል አቆጣጠር ከቀኑ 2:30 PM እስከ 5:30 PM) በቡሪያን ኪንግ ካውንቲ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ሁለንተናዊ አዳራሽ በመገኘት መሳተፍ እንደሚችሉ ጥሪው ያመለክታል።

በዚህ ታላቅ መርሃ ግብር ላይ የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ባለቤት ወይዘሮ ትሁን ወልዴ እና የበኩር ልጃቸው እርሚሻ ጴጥሮስ በክብር እንግድነት የሚገኙ ሲሆን፣ ስለ ፋውንዴሽኑ የወደፊት ራዕይ፣ እቅዶች እና ስራዎች ሰፊ ገለጻ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። የመሰብሰቢያው ዋነኛ ዓላማም ማህበረሰቡን በጋራ ማገናኘት፣ ውይይት ማድረግ እና ለፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ፋውንዴሽን ቤተ-መጻሕፍት እንዲሁም ለባዮሎጂ ተማሪዎች የተዘጋጀውን የነፃ የትምህርት ዕድል ፈንድ ለመደገፍ አቅም ማሰባሰብ እንደሆነ ተገልጿል።

ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የአካዳሚክ ልቀትን ማረጋገጥ፣ በባዮሎጂ መስክ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ማድረግ፣ ሳይንሳዊ ፈጠራዎችን እና ምርምሮችን ማበረታታት እንዲሁም ዘላቂ የማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክቶችን መደገፍን ዋነኛ ተልዕኮው አድርጎ እንደተነሳ በመረጃው ላይ ተመልክቷል። በተጨማሪም ወጣቶችን፣ ሴቶችን እና በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን አቅም ማሳደግ ሌላው የፋውንዴሽኑ ግብ እንደሆነ ተጠቅሷል ።

ይህ መርሃ ግብር ለኢትዮጵያ ሰፊ የትምህርትና የማህበራዊ በጎ አሻራ ጥለው ላለፉት ምሁር ክብር ለመስጠት እና ስራዎቻቸውን በዘላቂነት ለማገዝ የሚፈልጉ ሁሉ እንዲገኙበት የተዘጋጀ በመሆኑ፣ መላው የሲያትል እና የአካባቢው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት በዚህ ታሪካዊና የበጎ አድራጎት መድረክ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ቀርቧል ።

18 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.