Logo
EBC
"በኢትዮጵያ የሚገኘው የተመድ ጽ/ቤት ዋና ግብ የኢትዮጵያ መንግሥትን ስትራቴጂ መደገፍ ነው" - የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
**************************

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ በኢትዮጵያ የሚገኘው የተመድ ጽሕፈት ቤት ዋና ግብ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማገልገል እና የኢትዮጵያ መንግሥትን ስትራቴጂ መደገፍ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዋና ጸሐፊው ኢትዮጵያ የተመድን 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ልዩ የቴምብር ስብስብ ይፋ ባደረገችበት መርሐ-ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሀገራት በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ተገቢ የሆነ ውክልና እንዲኖራቸው በሚያደርጉት ጥረት ከጎናቸው እንደሚቆሙ ገልጸዋል።

በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ ያለንበትን ዓለም እንዲያንጸባርቅ እና በአፍሪካ ላይ የደረሰውን ታሪካዊ በደል ለማረም በምክር ቤቱ የአፍሪካ ቋሚ ወንበር እንዲኖር ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን በድጋሚ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ አፍሪካን በመወከል ረገድ ያላትን ታሪካዊ ሚና የገለጹት ዋና ጸሐፊው፣ ለተባበሩት መንግሥታት ማሻሻያ እና ለአፍሪካ ቋሚ የፀጥታው ምክር ቤት ወንበር መኖር ተገቢ እና ትክክለኛ ጥያቄ እያቀረበች መሆኑን አስረድተዋል።

አዳጊ ሀገራት በተለይም የአፍሪካ ሀገራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ውሳኔ ሰጪ ሚና እንዲኖራቸው የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንሥተዋል።

የአፍሪካ ሀገራት እያሳዩ ያሉት ከፍተኛ የመቋቋም አቅም እና የኢኮኖሚ ስኬት፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ተገቢውን ውክልና ለማግኘት ብቁ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዛሬ ያስተዋወቀችው ልዩ ቴምብር ከ1945 ዓ.ም ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከናወኑትን ታላላቅ ሥራዎች ማለትም ግጭቶችን ከመከላከል እስከ ረሃብ መቅረፍ፣ የቅኝ ግዛት መጨረሻን ከማረጋገጥ እስከ ሰብአዊ መብቶችን ማስከበር ያሉትን እንድናስታውስ እንደሚጋብዝ ተናግረዋል።

በዛሬው ፈታኝ እና ተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም፣ የፍትህ እና የብልጽግና ተስፋ እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ አሁንም አስፈላጊ እና አጣዳፊ መሆኑን ያረጋገጡት ዋና ጸሐፊው፣ ኢትዮጵያ በዚህ ዓለም አቀፍ የጋራ ጉዞ ውስጥ ግንባር ቀደም ሀገር እንደምትሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

በሔዋን ጌታቸው
#ebc #ethiopia #un #un80

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.