Logo
YenetaTube
የአሜሪካ የስለላ መረጃ ኢራን ሰፊ የሚሳኤል አቅም እንዳላት አሳይቷል

የኢራን ጦር ‹‹ፈራርሷል›› በሚል በትራምፕ አስተዳደር በተደጋጋሚ የሚነገረውን መረጃ የሚቃረንና ቴህራን አሁንም ከፍተኛ የሚሳኤል አቅም እንዳላት የሚያሳዩ በሚስጥር የተያዙ የአሜሪካ የስለላ ግምገማዎች መውጣታቸውን አንድ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ከሆነ፤ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የተገኙ የስለላ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢራን በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ አቅራቢያ ከሚገኙ 33 የሚሳኤል ጣቢያዎች ውስጥ የ30ውን ኦፕሬሽናል አገልግሎት ዳግም ማግኘት ችላለች።

ግምገማውን በቅርበት የሚያውቁ ሰዎችን ጠቅሶ ጋዜጣው እንደገለጸው፤ኢራን አሁንም ከጦርነቱ በፊት የነበራትን የሚሳኤል ክምችት እና ተንቀሳቃሽ ማስወንጨፊያዎችን በግምት 70 በመቶ ያህሉን እንደያዘች ትገኛለች።

በተጨማሪም ግምገማው እንዳመለከተው፤በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙት የኢራን የምድር ውስጥ የሚሳኤል ማከማቻ እና ማስወንጨፊያ ተቋማት መካከል ወደ 90 በመቶ የሚጠጉት አሁን ላይ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ስራ ጀምረዋል።

የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ኦሊቪያ ዌልስ እንደተናገሩት፤ የኢራን መንግስት ያለው እውነታ ቀጣይነት እንደሌለው ያውቃል፤ እንዲሁም ኢራን ወታደራዊ አቅሟን መልሳ ገንብታለች ብሎ የሚያስብ ሰው ወይ የተሳሳተ ነው፣ አለዚያም ለኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ልሳን ነው ብለዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት ወር በኢራን ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ቀጣናዊ ውጥረቱ ተባብሷል፡፡

ይህም ቴህራን በእስራኤል እና በባህረ ሰላጤው የአሜሪካ ወዳጆች ላይ የአጸፋ እርምጃ እንድትወስድ እንዲሁም የሆርሙዝ የባህር ሰርጥ እንዲዘጋ ምክንያት ሆኗል።

በፓኪስታን አምባሳደራዊ ጥረት ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት በመጋቢት ወር ስራ ላይ ውሎ ነበር፡፡

ሆኖም በኢስላማባድ የተደረጉት ተከታታይ ንግግሮች ዘላቂ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም፤የተኩስ አቁም ስምምነቱ ቆይቶ በትራምፕ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢስላማባድ የተቋረጠውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማደስ እየሰራች ትገኛለች፤ ሆኖም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦርነቱን በዘላቂነት ለማቆም አሜሪካ ላቀረበችው የሰላም ሃሳብ ኢራን የሰጠችውን የቅርብ ጊዜ ምላሽ ‹‹ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው›› በማለት ውድቅ አድርገውታል።

ሀና ሰይፉ

23 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.