Logo
EBC
ፈረንሳይ ለአፍሪካ የ27 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ የኢንቨስትመንት ዕቅድ ይፋ አደረገች
****************************

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደ የ"Africa Forward" ጉባኤ ላይ፣ ከአፍሪካ አህጉር ጋር ያለውን ግንኙነት በአዲስ መልክ ለመቅረጽ ያለመ የ23 ቢሊዮን ዩሮ (27 ቢሊዮን ዶላር) የኢንቨስትመንት ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።

ይህ እርምጃ ፈረንሳይ ከቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ ጋር ያላት ግንኙነት እየቀነሰ በመጣበት ወቅት፣ ከእንግሊዝኛ ተናጋሪ አገራት ጋር ያለውን የንግድ ትስስር ለማጠናከር የወሰደችው እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።

ፕሬዝዳንት ማክሮን በመግለጫቸው አፍሪካ እና ፈረንሳይ የጋራ ዓላማ ያላቸው "የእኩልነት አጋሮች" መሆናቸውን ገልጸው፣ ከጠቅላላው የገንዘብ ጥቅል ውስጥ 14 ቢሊዮን ዩሮ የሚሆነው ከፈረንሳይ ኩባንያዎች የሚመነጭ ሲሆን፣ ቀሪው 9 ቢሊዮን ዩሮ ደግሞ ከአፍሪካ ኩባንያዎች የሚጠበቅ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህ ኢንቨስትመንት በዋናነት በኢነርጂ ሽግግር፣ በግብርና፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በባህር ላይ ፕሮጀክቶች እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ላይ የሚውል ይሆናል።

ይህ ግዙፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በአፍሪካ እና በፈረንሳይ 250,000 አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

"እኛ እዚህ የተገኘነው በአፍሪካ አህጉር ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ብቻ አይደለም፤ ታላላቅ አፍሪካውያን የንግድ መሪዎችም ወደ ፈረንሳይ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንፈልጋለን" ሲሉ ግንኙነቱ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን ያማከለ መሆኑን ገልጸዋል።

በጉባኤው ላይ አፍሪካዊው ባለጸጋ አልኮ ዳንጎቴን ጨምሮ የቶታል ኢነርጂ እና የኦሬንጅ ኩባንያዎች ከፍተኛ ሥራ አስፈፃሚዎች ተገኝተዋል። በመድረኩም የፈረንሳዩ የጭነት መርከብ ድርጅት (CMA CGM) የሞምባሳ ወደብን ለማዘመን የ700 ሚሊዮን ዩሮ ኢንቨስትመንት ለማድረግ ቃል ገብቷል።

ይህ ጉባኤ አውሮፓ ከቻይና እና ከአሜሪካ ጋር እየበረታ የመጣውን የጂኦፖለቲካዊ ፉክክር ተከትሎ ከአፍሪካ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ አጋርነት ለማጠናከር እያደረገች ያለችውን ጥረት እንደሚያንፀባርቅ አልጀዚራ ዘግቧል።
#africaforward #nairobisummit #investment #economy

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.