Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ኢራን ‹‹ከአሜሪካ ጎን የሚቆሙ አገራት በሆርሙዝ ሰርጥ ለማለፍ አስቸጋሪ ሁኔታ ይገጥማቸዋል›› አለች፡፡ በቅርቡ አሜሪካ በኢራን ፍላጎቶች ላይ ማእቀብ የጣለች ሲሆን መርከቦች በሆርሙዝ ሰርጥ ለማለፍ ሲሉ ለኢራን ክፍያ እንዳይፈፅሙ ማስጠንቀቂያ መስጠቷም ይታወሳል፡፡ እንዲሁም አሜሪካና ባህሬን የሆርሙዝ ሰርጥን ጉዳይ በተመለከተ ለተባባሩት መንግስታት ድርጅት ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ አስገብተዋል፡፡

ኤኤፍፒ ይህንን ረቂቅ እንደተመለከተው ገልፆ ዋነኛ ሀሳቡ ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ የጣለችውን እገዳ እንድታነሳ የሚያሳስብ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ለዚህ የኢራን ባለስልጣናት ዛሬ መልስ ሰጥተዋል፡፡ የኢራን ጦር ሀይል ቃል አቀባይ የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል መሀመድ አክራሚና ለኢሪን ሲናገሩ ‹‹አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን ማእቀብ የሚከተሉ አገራት በሆርሙዝ ሰርጥ ለማለፍ አስቸጋሪ ሁኔታ ይገጥማቸዋል፡፡›› ብለዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹እኛ በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ አዲስ ህጋዊና የደህንነት ስርአት መስርተናል፡፡

ስለዚህም ከአሁን አንስቶ ማንኛውም መርከብ ለማለፍ ከፈለገ ከእኛ ጋር መተባበር ይኖርበታል›› በማለት አስረድተዋል፡፡ አዲሱ ስርአት ተግባራዊ መሆን መጀመሩን ያስታወቁት ቃል አቀባዩ ይህም የኢኮኖሚ፣ የደህንነትና የፖለቲካ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው ገልፀዋል፡፡ በተመሳሳይ የኢራን ፓርላማ የብሄራዊ ደህንነት ኮሚሽን ሀላፊ የሆኑት ኢብራሂም አዚዝ በኤክስ ገፃቸው ላይ ‹‹ባህሬንን የመሳሰሉ ጥቃቅን አገራትን ጨምሮ ሁሉም ከአሜሪካ ማእቀብ ጎን የሚሰለፉ መንግስታት መጥፎ መዘዝ እንደሚገጥማቸው ለማስጠንቀቅ እንፈልጋለን፡፡ ሆርሙዝ ሰርጥ ወሳኝ የህይወት መስመር በመሆኑ በራሳችሁ ላይ እስከናካቴው እንዲዘጋ የሚያደርግ አደጋ እንዳትፈጥሩ አሳስባለሁ›› ብለዋል፡፡

26 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.