Logo
FastMereja
የአንጋፋው ፖለቲከኛ ሌንጮ ለታን የግማሽ ክፍለ ዘመን ጉዞ የሚዳስስ መጽሐፍ ሊመረቅ ነው።

​#fastmereja I አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ሌንጮ ለታ ላለፉት 50 ዓመታት በኦሮሞ ብሔራዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የነበራቸውን ሚና እና ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚያዘክር ልዩ የክብር መርሃ ግብር ግንቦት 2 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል እንደሚካሄድ ተገለጸ።

​በዕለቱ የፖለቲከኛው የሕይወት ታሪክ ላይ የሚያተኩርና በደራሲ ዙፋን ኡርጋ የተሰናዳ "የሌንጮ ለታ የሕይወት ታሪክ" መጽሐፍ በኦሮምኛና በአማርኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ለንባብ እንደሚበቃ የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

​ይህ መርሃ ግብር በዋናነት ሦስት ዓላማዎችን ያሰነቀ ሲሆን፥ የመጀመሪያው የአቶ ሌንጮ ለታን የትግል ሕይወት ማክበርና ለኦሮሞ የፖለቲካ ትግል ዕድገት የነበራቸውን ፋና ወጊነት ዕውቅና መስጠት ነው።

ሁለተኛው ዓላማ የሌንጮ ለታን ፍልስፍናዊና ፖለቲካዊ ሐሳቦች፣ በተለይም በብሔርተኝነት፣ በሀገራዊ ግንባታ እና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ጥልቅ ትንታኔ የሚዳስስ ምሁራዊ መድረክ መፍጠር እንደሆነ ተገልጿል። በሦስተኛ ደረጃ መርሃ ግብሩ የፖለቲካ ትግሉን ሰብዓዊ ገጽታ ለማሳየት ያለመ ሲሆን፣ ይህም የአቶ ሌንጮን ቤተሰባዊ ሕይወትና ከትግሉ ጋር የነበረውን መስተጋብር የሚቃኝ ይሆናል።

​በዝግጅቱ ላይ የፎቶ ኤግዚቢሽን፣ የፓናል ውይይት፣ የቤተሰብ አባላት ምስክርነት እና የመጽሐፍ ዳሰሳ የሚቀርብ ሲሆን፥ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አንጋፋ ታጋዮች፣ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.