Logo
EBC
የአፍሪካ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ዛሬ ይጀመራል
*******************
የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ እና አህጉሪቱ የዲጂታል ትርክቷን በባለቤትነት እንድትመራ ያለመው የመጀመሪያው የአፍሪካ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS 2026) ዛሬ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ይጀመራል።

በፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ እና በኤጂኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ ትብብር በተዘጋጀው በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ፤ ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ይሳተፋሉ፡፡

በጉባኤው በድምሩ 321 ሚሊዮን ተከታይ ያላቸው 61 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ እንዲሁም 150 ሚሊዮን ተከታዮች ያሏቸው 120 ኢትዮጵያውያን የይዘት ፈጣሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ ከ470 ሚሊዮን በላይ የዲጂታል ተከታዮች ያላቸው እነዚህ ተሳታፊዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) በመጠቀም ይዘት በመፍጠር የወደፊት የአፍሪካ ሁኔታን ለማሳየት በዲፕሎማሲ ማዕከሏ አዲስ አበባ ላይ ተሰባስበዋል።

ይህ ጉባኤ አፍሪካ የራሷን ታሪክ ራሷ መተረክ የጀመረችበት አዲስ ዘመን ማሳያ ሲሆን፣ የተዛባውን የአፍሪካ ትርክት በእውነተኛ የአፍሪካ የዕድገት ታሪኮች ለመተካት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ተጠቅሷል።

በመድረኩ የይዘት ፈጣሪዎች የልምድ ልውውጥ ከማድረጋቸውም ባሻገር፤ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) አጠቃቀም፣ የአፍሪካን አዎንታዊ ገጽታ በመገንባት እና የዲጂታል ተጽዕኖን ከአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳ ጋር በማጣጣም ዙሪያ የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ።

የተጽዕኖ ፈጣሪዎቹ ስብስብ የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ከማሳየት ባለፈ፣ የኢትዮጵያን ቱሪዝምና ማራኪ ገጽታ በተለየ ሁኔታ ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል የፈጠረ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።
#ethiopia #africa #panafricanism

29 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.