Logo
FastMereja
ዲኬ ሆልዲንግስ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬን እያዳነ መሆኑን ገለጸ
#fastmereja I በአራተኛው ዙር "የኢትዮጵያ ታምርት" ኤክስፖ ላይ የተሳተፈው ዲኬ ሆልዲንግስ (DK Holdings)፣ ትራክተሮችንና የግብርና መሣሪያዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ መተካት መቻሉን አስታወቀ። ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ምርቶቹን እስከ 70 በመቶ የሚደርስ የሀገር ውስጥ ግብዓት በመጠቀም እያመረተ ይገኛል።

የኩባንያው ተወካይ አቶ ታረቀኝ ይልማ ለፋስት መረጃ እንደገለጹት፣ ድርጅቱ በግብርናው ዘርፍ ያለውን የቴክኖሎጂ ክፍተት ለመሙላት ሚዛን አማን ላይ ግዙፍ የትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ እየገነባ ነው። ከትራክተር ባሻገር እንደ ማረሻ፣ መከትከቻ፣ የበቆሎ መፈልፈያ እና መውቂያ ያሉ የግብርና መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ ባለሙያዎችና ማሽነሪዎች እያመረተ ለገበሬው እያቀረበ ይገኛል።

ኩባንያው የኤሌክትሪክ ፍጆታን የሚቆጥቡና የክልሎችን ባህላዊ እሴት የሚያንፀባርቁ "ስማርት ፖሎችን" (ዘመናዊ የጎዳና መብራት ምሶሶዎች) በማምረት በጎንደር፣ በሚዛንና በቢሾፍቱ ከተሞች ተግባራዊ አድርጓል።

ቀደም ሲል 100 ፐርሰንት ከውጭ ይገቡ የነበሩ ትራንስፎርመሮችን የሀገሪቱን የጥራት ደረጃ በጠበቀ መልኩ በሀገር ውስጥ እያመረተ ነው። ለከተማ ውበትና ለጽዳት አገልግሎት የሚውሉ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ጋንዳዎችን በስፋት እያቀረበ ይገኛል።

ዲኬ ሆልዲንግስ እነዚህን ምርቶች በሀገር ውስጥ ማምረቱ በከፍተኛ ዶላር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ረገድ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑንና በቀጣይም የኢንዱስትሪ ማሽኖችን የመገጣጠም እና የመተከል ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.