Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የ2025 የ'ሚስ ወርልድ አፍሪካ' የቁንጅና ዘውድ ባለቤቷ ኢትዮጵያዊት ሀሴት ደረጄ፣ "ሆፕ ፎር ዘ ፋዘርለስ" የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት ባዘጋጀው ዓመታዊ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ ከ7.8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዲሰበሰብ የበኩሏን አስተዋጽኦ አበረከተች።

ሀሴት በድርጅቱ ዓመታዊ የ'ሆፕ ናይት' ዝግጅት ላይ የመድረክ መሪ በመሆን ያገለገለች ሲሆን፣ በዕለቱም ከታቀደው 7.8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጻለች። ይህ ስኬት "ውበት ከዓላማ ጋር" ለሚለው መርህ ትክክለኛ ማሳያዋ መሆኑንም አስታውቃለች። በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው በጨረታ እና በተለያዩ መንገዶች የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉ እና የህፃናቱን ህይወት ለመቀየር ለተባበሩ አካላትም የላቀ ምስጋናዋን አቅርባለች።

በተጨማሪም የድርጅቱን መስራች እና መሪ 'አጎቴ ቤን' በማለት ጠቅሳ፣ የሰዎችን ህመም እንደራሱ አድርጎ የሚሸከምበትን ሰብዓዊነት እና ጥንካሬ በማድነቅ፤ የገነባው ተቋም ከድርጅትነት ባለፈ ለብዙ ህፃናት መኖሪያ ቤት፣ አባት እና የነገ ተስፋ መሆኑን መስክራለች።

እሷን ወደዚህ በጎ አድራጎት ቤተሰብ ለቀላቀለቻት ናኦሚ፣ እንዲሁም ለበጎ ፈቃደኞች እና የቡድን አባላት ምስጋናዋን ያቀረበችው ሀሴት፤ ስራው ገና ጅማሬ መሆኑን፣ ብዙ የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ እና ወደፊትም የሁሉንም ሰው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚፈልጉ አሳስባለች።

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.