Logo
Getu Temesgen
አዲስ አበባን የአህጉሪቱ የሥነ-ፈጠራ ማዕከል ያደርጋል የተባለው ፌስቲቫል ሊደረግ ነው
#ethiopia |​ "የሥነ-ፈጠራ ጥበባት ለለውጥ" በሚል መሪ ቃል የክራፍት አዲስ ፌስቲቫል ከሚያዝያ 22 እስከ 24 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ፌስቲቫሉ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እንደሚካሄድ በዛሬዉ እለት በተሰጠ መግለጫ ተገልጿል።

ይህ መድረክ ዓላማው የአፍሪካን የሥነ-ፈጠራ ኢንዱስትሪ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ አቅም መቀየር እንደሆነ ተገልጿል።

ዘሌማን በአፍሪካ የሥነ-ፈጠራ ዘርፍ ያለውን የ20 ዓመታት ልምድ በመጠቀም ያዘጋጀው ይህ ፌስቲቫል፣ ከመደበኛ ትርኢቶች ባለፈ የገበያ ተደራሽነት እና የቢዝነስ ትስስር ላይ ትኩረት እንደሚያረግ ነዉ የተገለፀዉ።

የዘሌማን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘላለም ወልደማርያም እንደገለጹት “የክራፍት ዋነኛ ግብ የአፍሪካን የፈጠራ ምናብ ከተሰጥኦ ወደ ተቋም፣ ከሥነ-ፈጠራ ደግሞ ወደ ዘላቂ ብልጽግና የሚያሸጋግሩ መንገዶችን መገንባት ነው'' ብለዋል።

ፌስቲቫሉ ከ10,000 በላይ ተሳታፊዎችን በአካል፣ ከ3 እስከ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን ደግሞ በዲጂታል አማራጮች ተደራሽ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

አዲስ አበባን በአህጉሪቱ እያደገ የመጣው የሥነ-ፈጠራ ማዕከል የማድረግ ራዕይን እንደሚያሳካ ነዉ የተገለፀዉ።

የዘንድሮው ፌስቲቫል ልዩ ትኩረት የሚሰጠው የኢትዮ-ጃዝ አባት በሆኑት በክቡር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ ለሚቀርበው የክብር ኮንሰርት ነው።

ዶክተር ሙላቱ 10 አባላት ያሉትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆነውን የ'Steps Ahead' ባንዳቸውን ከለንደን በማምጣት ታሪካዊ የሙዚቃ ድግስ የሚያቀርቡ መሆኑም በመግለጫዉ ተገልጿል።

ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ መርሃ-ግብር ላይ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (Al)፣ በኢንቨስትመንት እና በሥነ-ፈጠራ ኢኮኖሚ ዙሪያ የፓናል ውይይቶች፣ ይደረጋሉ።

በፋሽን፣ በፊልም፣ በዲጂታል ጥበባት (AR/VR) እና በቪዲዮ ጨዋታዎች (Gaming) ላይ ያተኮሩ ማስተር ክላሶች የሚቀርቡ ይሆናል ተብሏል።

ዝግጅቱ በመጨረሻው ቀን የአዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻዎች እና የፈጠራ ማዕከላትን በሚያስጎበኝ ልዩ የከተማ ጉብኝት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ተነግሯል።

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.