Logo
YenetaTube
የሴኔጋል መንግስት በግብረ ሰዶማዊነት ላይ ጠንካራ እርምጃ የሚወስድ አዲስ ህግ አፀደቀ።

የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ በሀገሪቱ ግብረ ሰዶማውያንን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀጣ አዲስ ህግ በፊርማቸው አፅድቀዋል።

ይህ አዲስ ህግ ቀደም ሲል በግብረ ሰዶማዊነት ድርጊት ላይ ተጥሎ የነበረውን ከፍተኛ የእስር ቅጣት ወደ 10 ዓመት ከፍ አድርጎታል።

" ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ድርጊቶች " ተብለው የተመደቡ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነቶች ላይ የሚጣለው ቅጣት ከነበረበት 1-5 ዓመት ወደ 5-10 ዓመት ከፍ እንዲል ተደርጓል።

አዲሱ ህግ ከእስር በተጨማሪ ከ2 ሚሊዮን እስከ 10 ሚሊዮን የሴኔጋል ፍራንክ ($3,500 - $17,600) የሚደርስ ከፍተኛ የገንዘብ መቀጮ ደንግጓል። ይህም ቀደም ሲል ከነበረው (1.5 ሚሊዮን ፍራንክ) እጅግ የላቀ ነው።

ግብረ ሰዶማዊነትን የሚያስተዋውቁ ወይም የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦች ከ3 እስከ 7 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ህጉ ይፈቅዳል።

አፀያፊ የተባለውን ይህን ድርጊት የሚያበረታታ ማንኛውም ድርጊት እንደ ወንጀል እንዲታይ ተደርጓል።

ህጉ ያለምንም ማስረጃ ሌላውን ሰው በግብረ ሰዶማዊነት ወንጀል የሚከስ ማንኛውንም አካል በወንጀል እንደሚቀጣ አካቷል።

ይህ ጠንካራ ህግ ፕሬዝዳንት ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ እና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኡስማን ሶንኮ በምርጫ ወቅት ለህዝባቸው የገቡትን ቃል የፈጸሙበት ነው ተብሏል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ውሳኔውን " እጅግ አሳሳቢ " ሲሉ የገለጹት ሲሆን ህጉ ሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ መሆኑን ተናግረዋል።

በተቃራኒው በሴኔጋል የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት እና ማህበራት ግብረ ሰዶማዊነት "የምዕራባውያን ባህል መጫኛ መሳሪያ ነው" በሚል ጠንካራ ቅጣት እንዲጣል ሲወተውቱ ቆይተዋል ተብሏል።

ከባለፈው የካቲት ወር ጀምሮ በሴኔጋል በርካታ ሰዎች በግብረ ሰዶማዊነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

አዲሱ ህግ ተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚጣለውን ቅጣት የበለጠ በማክበድ በሀገሪቱ ያለውን ጥብቅ ቁጥጥር የሚያጠናክር ነው።

በተለይም ድርጊቱ የተፈጸመው ለአካለ መጠን ባልደረሱ ህፃናት ላይ ከሆነ ከፍተኛው ቅጣት እንደሚተገበር ህጉ ይገልጻል።

tikvahethiopia

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.