Logo
YenetaTube
በትራምፕ ማስጠንቀቂያና በቢ-1 ድልድይ መፍረስ የተቀሰቀሰው የኢራንና አሜሪካ የአጸፋ ምላሽ ውጥረት

የኔታ ሚዲያ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሽንግተን በኢራን ላይ የጀመረችውን ጥቃት እንደምታሰፋና ቀሪ መሠረተ ልማቶችን እንደምታወድም ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ፣ ኢራን ድርጊቱን የጠላት "የሞራል ውድቀት" ስትል ኮነነች።

ትራምፕ በማህበራዊ ገጽ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ቴህራንን ከካራጅ ጋር የሚያገናኘውና ዘንድሮ ሊመረቅ የነበረው ግዙፉ የቢ-1 (B1) ድልድይ በአሜሪካ ጥቃት መፈራረሱን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማጋራት፣ በቀጣይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችና ሌሎች ድልድዮች ኢላማ እንደሚሆኑ ዝተዋል።

በድልድዩ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት 8 ሰዎች ሲገደሉ 95 የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸው የተነገረ ሲሆን፣ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በበኩላቸው ሲቪል ተቋማትን ማጥቃት ኢራናውያንን ለአሜሪካ እጅ እንዲሰጡ እንደማያደርጋቸውና ይህም የጠላት ሽንፈት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና እስራኤልና አሜሪካ ከፍተኛ የኢራን ወታደራዊ መኮንኖችን የማጥቃት እርምጃቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ የኢራን አብዮታዊ ዘበኛ የባህር ኃይል ደህንነት ምክትል ኃላፊ በህናም ረዛይ መገደላቸው ተረጋግጧል። ጦርነቱ አምስተኛ ሳምንቱን በያዘበት በዚህ ወቅት፣ በሆርሙዝ የንግድ መስመር አካባቢ ያለው አለመረጋጋት በዓለም አቀፉ የኢነርጂ ገበያ ላይ ከፍተኛ ስጋት የፈጠረ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የባህር መስመሩን ክፍት ለማድረግ "የመከላከያ እርምጃዎችን" ስለመጠቀም በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ሊመክር መሆኑ ታውቋል።

ኢራንም ለተሰነዘረባት ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ በመግለጥ፣ በኩዌት ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ዮርዳኖስ የሚገኙ ዋና ዋና ድልድዮችንና የኢንዱስትሪ ተቋማትን ዝርዝር ይፋ አድርጋለች።

ቀደም ሲልም በባህሬንና አቡዳቢ በሚገኝ የአሉሚኒየም እና የብረት ፋብሪካዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ያስታወሰችው ኢራን፣ የአሜሪካ ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ በቀጣይ የምትወስደው እርምጃ እጅግ የበረታ እንደሚሆን አስጠንቅቃለች።

በተጨማሪም የአሜሪካና እስራኤል ጥቃት እንደ ኮቪድ-19 ያሉ ወረርሽኞችን የሚከላከልውን የኢራን ፓስተር ኢንስቲትዩት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ የኢራን ጤና ሚኒስቴር ይህ ድርጊት በዓለም አቀፍ የጤና ደህንነት ላይ የተሰነዘረ ቀጥተኛ ጥቃት ነው በማለት የዓለም ጤና ድርጅትና ቀይ መስቀል ጉዳቱን እንዲያጠኑ ጥሪ አቅርቧል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.