Logo
FastMereja
አዲስ አበባ የአፍሪካ የመጀመሪያውን የሲቲ ማውንቴን ባይክ ኤሊሚኔተር ፕሮ ሊግ ልታካሂድ ነው!
#fastmereja I በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካን አህጉር የሚወክል የከተማ ማውንቴንባይክ ውድድር (City Mountainbike Eliminator Pro League) በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ በዛሬዉ እለት በተሰጠ መግለጫ ተገለፀ።

ሚያዝያ 24 እና 25 ቀን 2018 ዓ.ም በታሪካዊው የፒያሳ አድዋ ድል መታሰቢያ ሙዝየም ዙሪያ የሚካሄደው ይህ ውድድር፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ አዲስ ምዕራፍ ላይ እንደሚያስቀምጣት ተገልጿል።

ይህ በዓለም አቀፉ የብስክሌት ህብረት (ሀCI) ዕውቅና ያገኘው ውድድር፣ በጆርካ ኢቨንት እና በኢትዮጵያ ሳይክል ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚከናወን ሲሆን፤ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ መስተዳድር የዝግጅቱ ዋና ደጋፊዎች መሆናቸዉ ነዉ የተገለፀዉ።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ስፖርታዊ ኩነት ላይ ከ24 የአውሮፓ እና ከ10 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ከ60 እስከ 80 የሚደርሱ እውቅ (Elite) ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን ውድድሩ በሁለት ዋና ዋና ዘርፎች ማለትም ጥሎ ማለፍ-ኤሊሚኔተር እና ሾርት ትራክ የሚካሄድ ሲሆን፣ በሁለቱም ፆታዎች የሚደረግ ይሆናል፡፡

ቅዳሜ ሚያዝያ 24 የአማተር እና የልጆች የሰዓት ውድድሮች ሲሆን እሁድ ሚያዝያ 25 የኤሊት (Elite) ተወዳዳሪዎች የጊዜ ሙከራ፣ የጥሎ ማለፍ ዙሮች እና ታላቁ ፍፃሜ የሚካሄድ ይሆናል።

ከስፖርታዊ ፋይዳው አንጻር ዝግጅቱ ለሀገር ውስጥ ብስክሌተኞች በሀገራቸው ምድር ከዓለም ኮከቦች ጋር የሚፎካከሩበትን ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ ወደ ዓለም አቀፍ የውድድር ካላንደር ለመግባት አቋራጭ መንገድ እንደሚሆን ተጠቅሷል።

ይህ ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን የሚያገኝ ሲሆን፣ ወደ 2ዐ ሚሊዮን የሚጠጉ ተመልካቾች በቀጥታ እንደሚከታተሉት የሚጠበቅ ሲሆን ይህም አዲስ አበባ ያላትን የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት እምቅ አቅም ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.