Logo
Getu Temesgen
ገንዘብ አልሰጠኸኝም በሚል አባቱን የገደለው ግለሰብ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ
#ethiopia | በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካፋ ዞን፣ የገንዘብ ጥያቄ በማንሳት የ60 ዓመት ወላጅ አባቱን ደብድቦ የገደለው ግለሰብ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነ።

ወንጀሉ የተፈጸመው በዞኑ ገዋታ ወረዳ፣ ዶማ ቀበሌ ውስጥ ህዳር 3 ቀን 2018 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ላይ መሆኑን ፖሊስ አረጋግጧል። ተከሳሽ ሀብታሙ ዳጤ "ቡና ለቅሜ እና የእንጨት ማገዶ ሸጬ ያገኘሁትን ገንዘብ አልሰጠኸኝም" በሚል ሰበብ ከወላጅ አባቱ ጋር ግጭት ውስጥ ይገባል።

ይህንኑ ተከትሎም በመኖሪያ ቤታቸው ደጅ ላይ በባህር ዛፍ ዱላ የ60 ዓመት አባቱን ጭንቅላት ላይ በጭካኔ በመደብደብ ከባድ ጉዳት ያደርስባቸዋል። አባትየው ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ህክምና ተቋም ቢወሰዱም፣ በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ምክንያት ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።

ይህን አሳዛኝ ድርጊት ተከትሎም፣ የካፋ ዞን ዐቃቤ ህግ በፖሊስ የምርመራ መዝገብ ላይ ተመስርቶ ግለሰቡ ላይ የሰው ግድያ ወንጀል ክስ በመመስረት ለካፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦታል።

ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የካፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም፣ የቀረበለትን የዐቃቤ ህግ ማስረጃ እና የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ ተከሳሹን ጥፋተኛ ብሎታል።

በመሆኑም መጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም. በዋለው የወንጀል ችሎት፣ ጥፋተኛው ሀብታሙ ዳጤ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የቅጣት ውሳኔ ማሳለፉን ዐቃቤ ህግ ዮናስ ተረፈ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን አብራርተዋል።

(የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ፖሊስ ኮሚሽን ነው)

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ካፋ #ወንጀልና_ቅጣት #የደቡብ_ምዕራብ_ኢትዮጵያ_ፖሊስ #ኢትዮጵያ_ዜና #kafazone #ethiopiannews

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.