Logo
YenetaTube
በሌሊት መጥቶ ከጌታችን የተማረው መምህር 🙏

በዮሐንስ 3÷1-12 እንደተጻፈው የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት ስለኒቆዲሞስ ስብእና የሚነገርበት ነው። ኒቆዲሞስ መምህር ሲሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ የተማረ፣ የትህትና አርአያ በመሆኑ፣ ልቡናውን ከፍ በማድረግ ከፈሪሳውያን ህብረት ወጥቶ በትህትና ወንጌልን ለመማር በሃይማኖት ልቡናውን ለእግዚአብሔር ቃል በማዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ ከአይሁድ አለቆችና መምህራና አንዱ ቢሆንም በሌሊት ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየሄደ ስለ ሚስጥረ ጥምቀት፣ ሚስጥረ ሥላሴ፣ ሚስጥረ ሥጋዌና ሚስጥረ ትንሳኤ ሙታን በመማር ለትጋት አብነት መሆኑ ይነገርለታል፡፡ አይሁድ ጌታችንን ለማሰርና ለመግደል ሲዶልቱ ማንንም ሳይፈራ “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” ብሎ ተከራክሯቸዋል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር የአይሁድ አለቃ የሚሆን ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው በሌሊት መጣ፤ ስለምን በሌሊት መጣ ቢሉ “አንተ የአይሁድ አለቃ ስትሆን እንዴት ትማራለህ?” ደግሞም አላዋቂ እንዳይባል ሰው በማይመጣበት ሰዓተ ሌሊት ሊማር መጣ። አንድም ምሁረ ኦሪት ነውና ምሥጢር ሊያደላድል ነው። በቀን ጌታን አምስት ገበያ ሕዝብ ይከተለው ስለነበር ለመጠየቅ አልተመቸውም፡፡ ለጌታችንም እስከ መጨረሻው በመታመን በቀራንዮ ተግኝቶ ስጋውን ለመቅበር መብቃቱ ከኒቆዲሞስ ሕይወት ከምንማራቸው ድንቅ አብነቶች አንዱ ነው። ሌሊት በመከራ ይመሰላል፤ እናም በመከራ መጥቶ የተማረው ኒቆዲሞስ ሐዋርያት እንኳን ጥለውት በሸሹ ጊዜ ከመስቀሉ ሥር ተገኘ።

ኒቆዲሞስ በሌሊት መጥቶ ከጌታችን እግር ሥር ተቀምጦ ሲማር በዓይነ ኅሊናችን እንመልከተው! ግርማ ሌሊቱ ጸብአ አራዊቱ ሳያስፈራው፣ ድካም ሳይበግረው ሰው እንዳያየው ተደብቆ የመጣው ኒቆዲሞስ ከመስቀሉ ሥር የሚገኝ የመከራ ቀን ሐዋርያ ቢሆን ሥጦታ ይሆን ዘንድ የክርስቶስን ሥጋ ገንዞ ለመቅበር አበቃው። በመስቀል ላይ ቅድስት ነፍሱ ከቅዱስ ስጋው ስትለይ አውርዶ የሚቀብረው በሌለበት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ስታለቅስ የተገኘ የእመብርሃንን እንባ ያበሰ ቅዱስ ለመሆን በቃ። ኒቆዲሞስ የኃጢአት ምሳሌ በሆነው ጨለማ መምጣቱ በኃጢአት እንዳለ ንስሃ እንደሚፈግ ያስረዳናል፡፡ ዛሬም ቅዱስ ቃሉን ስንሰማ ለንስሃ እንዘጋጅ፡፡ ገዳማውያን የወንጌሉን ቃል ሰምተው በንስሃ ይመላለሳሉ፣ በጸሎትም ይተጋሉ ገዳማቸውን እንደግፍ በዓታቸውን እናጽና፡፡

ድጋፍ ለማድረግ፦ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.