Logo
FastMereja
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ማህበረሰቦች እና ሴት ስራ ፈጣሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ታላቁ የማይክሮ ፋይናንስ ኮንፈረንስ ተጀመረ!
#fastmereja :የኢትዮጵያ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማህበር (AEMFI) ከአውሮፓ ህብረት (Eሀ) እና ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የነገው ትውልድ ማይክሮ ፋይናንስ ኮንፈረንስ በዛሬዉ እለት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ከመጋቢት 15 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የስብሰባ ማዕከል በሚቆየው በዚህ ጉባኤ ላይ፤ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የፋይናንስ ዘርፍ መሪዎች፣ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

“ዕድሎችን በፈጠራ፣ በአካታችነት እና በማገገም አቅም ባላቸው የፋይናንስ አገልግሎቶች መክፈት'' በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ኮንፈረንስ፣ በዋናነት ዲጂታል ፈጠራዎች እና የፖሊሲ ማሻሻያዎች የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት ያላቸውን ሚና ይፈትሻል።

በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ማህበረሰቦች እና ሴት ስራ ፈጣሪዎች የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑና የኢኮኖሚ ጥንካሬ እንዲገነቡ በሚያስችሉ መንገዶች ላይ ሰፊ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየዉ ጉባኤ ውስጥም የከፍተኛ የፋይናንስ ባለሙያዎች የፓናል ውይይቶች፣በፈጠራ የታጀቡ የፋይናንስ መፍትሄዎች ገለጻዎች፣እንዲሁም የፊንቴክ (Fintech) እና የማይክሮ ፋይናንስ ውጤቶች የሚቀርቡበት ኤግዚቢሽን እንደሚካሄድም ነዉ የተገለፀዉ።

ይህ ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉን ለማዘመንና አካታች ለማድረግ በምታደርገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ያላቸውን ሚና ለማጎልበት ያለመ ነው፡፡

ይህ ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉን ለማዘመንና አካታች ለማድረግ በምታደርገው ጥረት ውስጥ እንደ ትልቅ ምዕራፍ የሚቆጠር መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተለይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ዘመናዊ አሰራሮችን በመከተል የገጠሩን ማህበረሰብ እና አነስተኛ የንግድ ዘርፎችን ወደ ፋይናንስ ስርዓቱ በማስገባት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ያላቸውን ድርሻ እንዲያሳድጉ ትልቅ መድረክ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

ኮንፈረንሱ እስከ መጋቢት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ሲሆን፣ በስተመጨረሻም በዘርፉ ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል።

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.