Logo
FastMereja
ከ564 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኘው የሆርቲካልቸር ዘርፍ ትልቅ ኩነት በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነዉ!
#fastmereja I አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ከኤች.ፒ.ፒ. ኤግዚቢሽን ወርልድዋይድ ጋር በመተባበር የተዘጋጀዉ 10ኛው ዓለምአቀፍ የሆርቲካልቸር የንግድ ትርዒት (ሆርቲፍሎራ ኤክስፖ 2026) ከመጋቢት 15 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለፀ።

በአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ንግድ ትርዒት ላይ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ከ50 በላይ ሀገራት የተወከሉ ከ150 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ አልሚ ባለሀብቶች፣ አምራቾች፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎችና የፋይናንስ ተቋማት እንደሚሳተፉ ነዉ የተገለፀዉ።

የሆርቲካልቸር ንዑስ ዘርፍ ከቡና ቀጥሎ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ዘርፍ ሲሆን፣ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 564.89 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ማድረጉ ነዉ የተገለፀዉ።

የዘንድሮው ኤክስፖ ልዩ የሚያደርገው፣ መንግሥት የ10 ዓመት ብሔራዊ የሆርቲካልቸር ልማት ስትራቴጂን እና የ15 ዓመቱን ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት መርሃግብር ይፋ ካደረገ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ ዓለምአቀፍ ሁነት መሆኑ ሲሆን ይህም ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም እና የወጪ ንግድ ገቢን የሚያሳድግ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ግንባታ ለማካሄድ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ ታላቅ ሁነት አምራቾችን፣ ላኪዎችን፣ ገዢዎችንና ፖሊሲ አውጪዎችን በአንድ ጣሪያ ስር በማገናኘት የኢትዮጵያን እምቅ አቅም ለዓለም ገበያ ይበልጥ ለማስተዋወቅና የንግድ ትስስርን ለማጠናከር ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.