Logo
FastMereja
አዋሽ ባንክ ሦስት አዳዲስ የዲጂታል መተግበሪያዎችን ስራ አስጀመረ

​#fastmereja I አዋሽ ባንክ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋት የነደፋቸውን ሦስት አዳዲስ የቴክኖሎጂ መተግበሪያዎች ዛሬ መጋቢት 03 ቀን 2018 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል በይፋ ስራ ማስጀመሩን አስታወቀ።

​ባንኩ ስራ ያስጀመራቸው ሦስቱ መተግበሪያዎች አዋሽ ረሚት (Awash Remit)፣ አዋሽ ኢ-ቲኬቲንግ (Awash E-Ticketing) እና አዋሽ ኢ-ፕሮፐርቲ ማኔጅመንት (Awash E-Property Management) የተሰኙ ናቸው።

​አዋሽ ረሚት በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው በቀጥታ፣ በፍጥነትና በደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ገንዘብ እንዲልኩ የሚያስችል ነው። ደንበኞች በቪዛ (Visa) ወይም በማስተር ካርድ (MasterCard) በመጠቀም በቀጥታ ወደ አዋሽ ባንክ ሂሳብ ወይም ወደ አዋሽ ብር ፕሮ (Awash Birr Pro) ገንዘብ ገቢ ማድረግ ይችላሉ።

​አዋሽ ኢ-ቲኬቲንግ ኮንሰርቶችን፣ ስፖርታዊ ኩነቶችንና የተለያዩ ስብሰባዎችን የሚያዘጋጁ አካላት ቲኬቶችን ሙሉ በሙሉ በኦንላይን እንዲሸጡና እንዲያስተዳድሩ ያስችላል። መተግበሪያው የወረቀት ቲኬቶችን በዲጂታል ኮድ (QR Code) የሚተካ በመሆኑ ለአዘጋጆችም ሆነ ለታዳሚዎች ከፍተኛ ምቾት ይሰጣል።

​አዋሽ ኢ-ፕሮፐርቲ ማኔጅመንት የህንፃ ባለቤቶችና ተከራዮች የኪራይ ውልን፣ የክፍያ ሁኔታንና የፋይናንስ ክትትልን በዲጂታል መንገድ እንዲያከናውኑ የተዘጋጀ ነው። መተግበሪያው የመኖሪያ ቤቶችን፣ የንግድ ቦታዎችንና የመኪና ማቆሚያዎችን በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር ይረዳል።

​አዋሽ ባንክ በመግለጫው እንዳመለከተው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሐምሌ እስከ ታኅሣሥ 2025 ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ በባንኩ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት የተከናወነው የገንዘብ ዝውውር መጠን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገልጿል።

​ባንኩ በቀጣይም የደንበኞቹን እርካታ ለማሳደግ ተጨማሪ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ለማልማት እየሰራ መሆኑን ገልጾ፣ ህብረተሰቡ እነዚህን አዳዲስ አገልግሎቶች እንዲጠቀም ጥሪ አቅርቧል።
#ቢዝነስ #ሳይ_ቴክ

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.