Logo
YenetaTube
ከብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞና አካባቢው ጎፋና ባስኬቶ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በጋሞ ዞነሰ ደጋማ አካባቢዎች በደረሰው የተፈጥሮ አደጋ ለጠፋው የሰው ሕይወት እና ላጋጠመው የንብረት ጉዳት የተሰማቸውን ኃዘን ገለጹ።

ብፁዕነታቸው የሰጡት መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል።

(ብፁዓን እለ ይላሕው ይእዜ እስመ እሙንቱ ይትፌሥሑ፡፡)
“የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው መፅናናትን ያገኛሉና፡፡'' (ማቴ.፭፤፬)

ትናንት በጋሞ ዞን በተለያዩ ደጋማ አካባቢዎች ማለትም በጋጮ ባባ ወረዳ ማዞ ዶይሳ ቀበሌ፣ በላካ፣ በቦንኬ ወረዳ የላ ቀበሌ እንዲሁም በከምባ ዙሪያ ወረዳ ባልታ ቀበሌዎች በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው የናዳና የጎርፍ አደጋ የ30 ወገኖቻችን ሕይወት ማለፉን፣ እንዲሁም በአርባ ምንጭ ከተማና ዙሪያው የኩልፎና ስጎ ወንዞች መሙላት በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን በታላቅ ሐዘን ሰምተናል።

ይህ ድንገተኛ አደጋ በወገኖቻችን ላይ ያደረሰው የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ለመላው የአካባቢው ነዋሪና ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ መርዶ ነው።በመሆኑም በራሴና በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ስም እንዲሁም በመላው የኦርቶዶክሳዊያን ምዕመናን ስም የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እንገልጻለን፡፡

በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ፈጣሪ አምላክ ነፍሳቸውን በገነት እንዲያሳርፍልን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጥ እንጸልያለን። በንብረታቸው ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችንም ፈጣሪ ጥንካሬውን እንዲሰጣቸው እንመኛለን፡፡

ሀገረ ስብከታችን ይህንን አስከፊ ወቅት ለማለፍና የተጎዱ ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ማንኛውም ዓይነት ሰብአዊ ድጋፍና መርሐ ግብሮች ላይየበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡።

መላው ሕዝባችንም የተጎዱትን በመርዳትና በማጽናናት የወንድማማችነትና የአብሮነት እናስተላልፋለን። የቆየውን እሴቱን በተግባር እንዲያሳይ ጥሪያችንን

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝባችንንና ምድራችንን ከክፉ መከራ ሁሉ ይጠብቅልን !!

ብፁዕ አቡነ ኤልያስ
የጋሞና አካባቢው፣ ጎፋና ባስኬቶ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል !!

መጋቢት 2 /2018 ዓ/ም አርባ ምንጭ

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.