Logo
FastMereja
ሜሪ ጆይ በአዲስ አበባ የኩላሊት እጥበት ማዕከል አስመረቀ
#fastmereja I ከተጀመረ 32 ዓመት ያስቆጠረው ሜሪ ጆይ አስኮ በሚገኘው ማዕከሉ የኩላሊት እጥበት ህክምና አገልግሎት ዛሬ የካቲት 20 2018 ዓ.ም አስመርቋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎች ፣የግሉ ዘርፍና የማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የተመረቀው ይህ ማዕከል በመከላከል ላይ ትኩረቱን ያደረገውን የጤና ፖሊሲ በመተግበር ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ተብሏል።

ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ለህክምና አገልግሎቱ እዚህ ደረጃ መድረስ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን አመስግነዋል።

ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የኩላሊት እጥበት ማዕከል በሀዋሣ ከተማ ከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። በቀጣይም በአርባ ምንጭ ፣ በደብረ ብርሀን፣በሆሳዕና ከተሞች የኩላሊት እጥበት አገልግሎት እንደሚጀመር ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ተናግረዋል።

ዛሬ አዲስ አበባ ላይ የተመረቀው የኩላሊት እጥበት ማዕከል 10 አልጋዎች ሲኖሩት በተመጣጣኝ ዋጋም አገልግሎት እንደሚሰጥ ተነግሯል።

በዕለቱ ሜሪ ጆይ ማዕከልን ለማገዝ ግለሰቦች ፣ የመንግሥት ኃላፊዎችና ተቋማት የክብር አባል ቅፅ የሞሉና ፊርማቸውን ያኖሩ ሲሆን ሌሎች ተቋማትም ትልቅ እገዛ ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በዕለቱ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሜሪ ጆይ እየሠራ የቆየው ተግባር ትልቅ ማህበራዊ ችግርን የሚቀርፍ መሆኑንም አመልክተዋል።

በዕለቱ ማዕከሉን ለማገዝ የክብር አባል ከሆኑት መካከል ካዲስኮ ፣ የጤና ጥበቃ ሚ/ር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ ወይዘሮ ጠይባ ሀሠን የስደትና ተመላሾች አገልግሎት ኮሚሽን ዳይሬክተር ጄነራል ፣ ዶክተር ሙልጌታ እንዳለ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣ ዶክተር አስቻለው የጤና ሚኒስትር አማካሪ ፣ጄነራል ሁሉአገርሽ ከመከላከያ፣ አዋጭ ብድርና ቁጠባ፣ ያኔት የጥርስ ህክምና የአርባ ምንጭ ከንቲባ ዶክተር መስፍን መንዛ ፣ የሆሳዕና ዞን አስተዳደር ከፍተኛ አማካሪ አቶ ታምራት አኑሎ፣ የቶቶት ምግብ ቤት ባለቤት አቶ ጠንክር ቴኒ ይገኙበታል።በተለያየ መልኩ እገዛ ለማድረግ ቃል የገቡ ሰዎችና ተቋማትም ከሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ጎን ለመሆን በጎ ፍቃደኝነታቸውን ገልፀዋል።
#ጤና መረጃ

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.