Logo
FastMereja
የወ/ሮ አስቴር መንገሻ አጭር የህይወት ታሪክ
በቀብር ስነስርዓታቸው ላይ ከተነበበው የተወሰደ ነው።

ወ/ሮ አስቴር መንገሻ ከአባታቸው ከአቶ መንገሻ ጫላ ከእናታቸው ከወ/ሮ ጌጤ ኩበክቤ በኦሮምያ ክልል በአዲስ አለም ኪሞዬ በኤጆሬ ወረዳ በ 1947 ዓ.ም ተወለዱ።

ወ/ሮ አስቴር ለአቅመ ሄዋን ሲበቁ በ1964 ዓ.ም ከውድ ባለቤታቸው ከአቶ ደፋር ቶላ ጋር ትዳር መስርተው የ 2 ወንድ እና የ 4 ሴት እናት ነበሩ ።
ወ/ሮ አስቴር ከ6 ልጆቻቸው ውስጥ አራተኛ ልጃቸው ለእሳቸውና ለባለቤታቸው ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ጀግናን የወለዱ ማህፀነ ለምለም ያስባለላቸው ናቸው።

በአራተኛ ልጃቸው በአትሌት መሰረት ደፋር በአለም አደባባይ ማለትም አለም በሚጠብቀው የትኛውም የዓለም ስፖርተኛ ህልሙና ዕውኑ በሆነው ኦሎምፒክ ላይ በ2004 በአቴንስ ኦሊምፒክ በ5000 ሜ ወርቅ በ2008 በቤጂንግ ኦሊምፒክ በ5000 ሜ ብር በ2012 በለንደን ኦሊምፒክ በ5000ሜ ወርቅ ያጠለቀች።

👉 በአለም ሻፒዮና 2 ወርቅ 1 ብር 2 ነሀስ ያጠለቀች፤
👉በ4 የአለም የቤት ውስጥ ሻፒዮናዎች ላይ በ3000ሜ 4 ወርቅ ያጠለቀች ፤
👉 በአለም ወጣቶች እና በአፍሪካ ሻንፒዮናዎች ላይ 3 ወርቅ 5 የብር ሜዳሊያዎችን ያጠለቀች፤
👉 በተጨማሪም በካሊፎርኒያ እና በቤልጅየም በተካሄዱ
የ 2 ማይል የሩጫ ውድድሮች የአለም ክብረ ወሰኖችን የሰበረች፤
👉 የአለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአመቱ ምርጥ አትሌት ዘርፍ ሽልማትን እ ኤ አ በ2007 ያሸነፈች ጀግና ወልደው ለኢትዮጵያ ህዝብ ያበረከቱ መልካም እናት ነበሩ!!

ማህፀነ ለምለሟ ወ/ሮ አስቴር በአትሌት መሠረት ደፋር እናትነት ይታወቁ እንጂ ሁሉንም ልጆቿቸውን ለማሳደግ እና ቦታ ለማስያዝ ብዙ ዋጋ እና መስዋእትነት የከፈሉ ሲሆን በዚህም ሌሎች ልጆቻቸው በሙሉ የህክምና ባለሙያ በመሆን ክሰዋቸዋል።

ወ/ሮ አስቴር መንገሻ በትዳር እና በቤተሰብ ህይወታቸው እጅግ ስኬታማ የሆኑ እናት ነበሩ ለ 54 አመታት በፍቅር እና በሰላም በኖሩበት ትዳራቸው የ18 የልጅ ልጆች አያት ለመሆን የበቁ ናቸው።

ወ/ሮ አስቴር በሰፈር አካባቢያቸው በተለይም ረጅም አመታት በኖሩበት በአዲስ አበባ አስኮ አካባቢ በማህበራዊ ኑሮአቸውም የተወደዱ እና የተከበሩ ያልወለዱአቸውን ልጆች ሁሉ የረዱ እና ያሳደጉ መልካም እና ደግ የሁሉ እናት ነበሩ።

ወ/ሮ አስቴር መንገሻ ባደረባቸው ህመም በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጪ ህክምናቸውን እየከታተሉ ቢቆዩም ከፈጣሪ ጥሪ የሚቀር የለም እና ወ/ሮ አስቴር መንገሻ በየካቲት 14 /2018 ዓ.ም በተወለዱ በ 71 አመታቸው ከዚህ ከአለም ድካም አርፈዋል ።

የቀብር ስነ ስርአታቸውም የካቲት 15/2018 ዓ.ም ቤተሰብ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሳ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።

ልዑል እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በአፀደ ገነት ያኑርልን ለቤተሰብ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ያድልልን።

በእናታችን ህምም ጊዜ ከእኛ ጋ በመሆን ላስታመማችሁ፤ ለጠየቃችሁ፤ በፀሎት ላሰባችሁን በሙሉ ፈጣሪ ያክብርልን በማለት ቤተሰቦቻቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዘገባው የEthio Runners ነው!

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.