Logo
Getu Temesgen
የህጻናት መብት እና የህግ ጥበቃ
በኢትዮጵያ እና በአለምአቀፍ ህግ ማእቀፍ

ጠበቃና የህግ አማካሪ ፋንታሁን ደለለው 0929101037,0983337690

መግቢያ #ethiopia | በሰው ልጆች የእድገት ደረጃ ህጻን ልጆች ልዩ ትኩረትና እንክብካቤ የሚሹ መሆኑን ብዙ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ህጻናት ከተዋለዱ ጀምሮ ራሳቸውን ማስተዳደር የማይችሉና ልዩ እንክብካቤ እና ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ያላቸውን የህግ ጥበቃ በመመልከት አስፈላጊውን የህግ ግንዛቤ ለማህበረሰቡ ለማድረስ የአለምአቀፍ ህግ ድንጋጌ፣ህገመንግስታችንን ፣የወንጀል፣ የፍ/ር ህግ እና ቤተሰብ ህጋችንን በመዳሰስ አስፈላጊ ናቸው ያልናቸውን በዚህ ጽሁፍ አስፍረናል።

1. ህጻን እንዴት ይተረጎማል?

በዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን አንቀጽ 1 የተመለከተው ዕድሜን መሠረት ያደረገ ትርጉም ሲሆን “ሕፃን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የሆነ የተፈጥሮ ሰው” እንደሆነ ይገልፃል፡፡ የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች እና ደኅንነት ቻርተር አንቀጽ 2 ሕፃን ለሚለው ትርጓሜ ሲሰጥ “ሕፃን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የሆነ የተፈጥሮ ሰው ነው” በማለት ደንግጓል፡፡

በኢትዮጵያ ለሕፃን ያለውን ትርጉም ስንመለከት ሀገሪቱ ፌደራላዊ ስርዓት የምትከተል በመሆኑ እና የ1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራስያዊ ሪፐብሉክ ሕገ መንግሥት የፌደራል እና የክልል መንግሥታት የየራሳቸውን የቤተሰብ ሕግ እንዲያወጡ ስለሚፈቅድ የተለያየ የሕፃን ትርጓሜ ሊኖር የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ በፌደራል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 215 መሠረት አካለ መጠን ያልደረሰ ሰው ማለት ጾታ ሳይለይ ዕድሜው አሥራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ልጅ ነው::

2. የህጻናት መብት መርሆዎች በ1959 በተባበሩት መንግስታት በወጣው የህጻናት መብት መግለጫ....

በአለምአቀፍ ህጎች ዋናውና መሠረታዊው የህጻናት መርህ "ሕፃናት ጥቅምና ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት (Best interest of the child) "የሚለው መርህ መሰረት በማድረግ አራት የህጻናት መርሆች የሚታወቁ ሲሆን እነዚህም
የእኩልነት መብት (The Non-discrimination clause) የኮንቬንሽኑ አንቀጽ 2
ለሕፃናት ጥቅምና ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት (The Best Interest of the Child) የኮንቬንሽኑ አንቀጽ 3)
የመሳተፍ መብት (The Right to participation) ኮንቬንሽኑ ።
አንቀጽ 12፣
በሕይወት የመኖር እና የመልካም አስተዳደግ መብት (The Right to life, survival and development) የኮንቬንሽኑ አንቀጽ 6፣ ናቸው

2. በሀገራችን ህጻናት ያሏቸው ህጋዊ መብቶች መካከል...

2.1 ህጻናት በጽንስ እያሉ ህግ የሰጣቸው መብት
የፍ/ር ህግ ቁጥር ድንጋጌ ላይ የተጸነሰ ልጅ እንደተወለደ እንደሚቆጠር ያስቀምጣል። ይህ ማለት ከውርስ ፣ ከህጻኑ ስጦታ ፣ ኑዛዜ መብቶች ጋር አስመልክቶ ለሚደረግለት እና ህግ ለሚጠብቅለት ነገር የተጸነሰው ልጅ እንደተወለደ ይቆጠራል:: ይሁን እንጂ አንድ ህጻን ተወልዶ እንደ ሰው የሚቆጠረው 48 ሰአት ሲሞላ ሲሆን ይህ በፍ/ህግ ቁጥር 4 ላይ የተቀመጠ ነው።

2.2 የውርስ መብት

በፍ/ር ህግ ቁጥር 826 መሠረት ሟች አባት ወይም አውራሽ ሲሞት ውርስ ተከፈተ ይባላል። በዚህን ጊዜ የእድሜ ልዩነት ሳይኖር በውርስ ካልተነቀለ በቀር ከ18 አመት በታች ያሉ ህጻናትም በፍ/ር ህግ 842 መሠረት አንድ ላይ ያለ ኑዛዜ ህጋዊ ወራሽ ይሆናሉ። ኑዛዜ የተተወላቸው ከሆነም በኑዛዜው መሰረት መብታቸው የሚጠበቅላቸው ይሆናል።

2.3 ንብረት የማፍራት የመጠበቅ መብት

ህጻናት በሞግዚታቸው ወይም በተመደበላቸው ጠባቂ አስተዳዳሪ አማካኝነት ንብረታቸውን የማፍረት ፣ የመጠበቅ የማስተዳደር ህገመንግስታዊ ጥበቃ ጭምር አላቸው። የኢፊድሪ ህገመንግስት አንቀጽ 36፥40 የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 269 እና ተከታዮቹ በተለይም አንቀጽ 280 መሠረት መብቶቻቸው የሚጠበቅላቸው ይሆናል።

2.4 በአሳዳጊ እና በሞግዚት የማደግ መብት

በፌደራል የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ መሠረት በአሳዳጊ ለጤንነታቸው እና ለእድገታቸው ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ አሳዳጊ እንዲኖራቸው ግድ ነው። ንብረታቸውን የሚያስተዳድር ደግሞ ሞግዚት እንዲኖራቸው መብታቸው ነው። አባት እና እናት እስካላቸው ድረስ ሞግዚትም አሳዳጊም እነሱ ናቸው። እንዱ በሌለ ወይሜ በሞተ ጊዜ ከእነርሱ ያለው አባትና ወይም እናት ይሆናል። ሁለቱም ከሌሉ በፍርድ ቤት የሚመደቡ ይሆናል። የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ 222፥226፥229 መሠረት ይህ መብት የሚጠበቅ ይሆናል።

2.5 እናትና አባትን የማወቅ መብት

በኢፊድሪ ህገመንግስት አንቀጽ 36 መሠረት እናትና አባትን የማወቅ መብት አላቸው።ዜግነት የማግኘት መብት፣
እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዲሁም ለእድገታቸው ለኑሮዋቸው የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ የማገኘት መብት አላቸው።

2.6 ቀለብ የማግኘት መብት

ህጻናት ለእድገታቸው ለኑሮአቸው አጠቃላይ ወጪ ትምህርት ጤንነት ጥበቃ ሳይቀር አስፈላጊውን ወጪ ከወላጆቻቸው እንዲመደብላቸው በህግ መብት ተሰጥቶዋቸዋል። ቀለብ በፌደራል የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 197 መሠረት ምግብ፣መጠለያ፣ልብስ፣አስተዳደግ፣ትምህርት ለልጁ የሚያስፈልገውን አጠቃላይ ወጪ ይሸፍናል። ይህ እስከሆነ ድረስ ወላጆች አሳዳጊዎች ይህን የማድረግ ግዴታ አለባቸው።

2.7 የጉዲፈቻ መብት

ህጽናት ለአስተዳደጋቸው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ (best interest of the child) በጉዲፈቻ እንደ አባት ወይም እናት ተድርጎ የሚቆጠር ጉዲፈቻ አድራጊ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ከዚህ ጉዲፈቻ ልጅ የተፈጥሮ ወላጆች ጋር የጉዲፈቻ ስምምነት ተደርጎ በፍርድ ቤት የሚጸድቅ በመፈጸም ጉዲፈቻ አድራጊው ተስማምቶ ከወሰደበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ልጁ ሆኖ እንደ ወላጅ የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደርግለታል። የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 180 እና 181 ላይ ተደንግጓል።

3. ህጽናት የወንጀል ጥፋት ሲፈጽሙ የሚታዩበት የህግ አግባብ
የኢፊድሪ ወንጀል ህግ ስለ ህጻናት መብት 157-168...

3.1 ህጻናት ከዘጠኝ አመት በታች ሲሆኑ ደግ ክፉዉን በአግባቡ ያለዩ በመሆኑ በወንጀል ሊጠየቁ እንደማይችሉ ህጉ ጥበቃ ያደርግላቸዋል።ነገር ግን ወላጆቻቸው በፍትሃብሔር ጉዳይ ላለው ኀላፊነት ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ።

3.2 ከዘጠኝ አመት እስከ አስራአምስት አመት የሆኑ ህጻናት...
እነዚህ ህጻናት ስነልቦናቸውን ሰብብአዊ መብታቸውን ከመጠበቅ አንጻር ልዩ የስኖልቦና፣የህግ ባለሙያ ድጋፍ ተደርጎላቸው የሚታይ ሲሆን በመደበኛው ስነስረአት የሚታይ አይደለም።

የሚተላለፍባቸው ውሳኔ እና ከጥፋታቸው ሊማሩ የሚችሉበት መንገድ እንደ እድሚያቸው ያገናዘበ ነው። ማረሚያ ቤት ከሚላኩ ይልክ በሌላ ተቋም ቦታ ወይም ፍርድ ቤቱ ባመነበት ልክ የሚፈጸም ሲሆን እንደ ጥፋቱ ክብደት በምክርና በተገሳጽ ሊታለፉ ይችላሉ። ይህ ለህጻናት የተሰጠ ልዩ መብት ነው።

ከአስራአምስት በላይ እስከ አስራ ስምንት አመት የሆኑትን በተመለከተም በመደበኛው አይነት የህግ ጉዳያቸው የሚታይ ቢሆንም በኢፊድሪ ወንጀል ህግ አንቀጽ 179 መሠረት ከቅጣት አንጻር የተለየ አስተያየት ይደረግላቸዋል። እድሜያቸውንም ባገናዘበ መልኩ ማረሚያ ቤቱ ቅጣቱን የሚያስፈጽም ይሆናል።

4. በህጻናት ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች የኢፊድሪ ወንጀል ህግ ያለው የህግ ጥበቃ

_ ሕፃን መግደል (አንቀጽ 544)
- በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካይነት በእርጉዝ ሴቶች እና ሕፃናት ህይወት ላይ ጉዳት ማድረስ( አንቀጽ 561)
- በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካይነት በእርጉዝ ሴቶች እና ሕፃናት አካል ላይ ጉዳት ማድረስ( አንቀጽ 562)
- ሰውን ለአደጋ ማጋለጥ ወይም መተው (በጤናው፣ በዕድሜው፣ በሁኔታው ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት ራሱን ለመጠበቅ የማይችለውን ሌላ ሰው ማለትም በእድሜው ምክንያት በሚለው ለሕፃናት ተፈፃሚ ስለሚሆን ... (አንቀጽ 574)
- ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን መጉዳት (ህፃናትን የሚመለከት) (አንቀጽ 576)
- ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን መጥለፍ (አንቀጽ 589)፣
- ሕጻንን ማለዋወጥ እና የራስ ያልሆነን ህጻን መውሰድ (አንቀጽ 591)፣
- ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን አለማቅረብ (በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ መሰረት ልጁን እንዲረከብ መብቱ ለሆነ ሰው ወይም ተቋም አላስረክብም ማለት (አንቀጽ 592 )፣
በግብረ ሥጋ ነፃነትና ንፅህና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በተመለከተ የሚከተሉት ተጠጠቅሰዋል
- ዕድሜያቸው አስራ ሶስት ዓመት በሆነና አስራ ስምንት ዓመት ባልሞላቸው ልጆች ላይ የሚፈጸም የግብረ ስጋ ድፍረት በደል (አንቀጽ 626) ፣
- በህፃናት ልጆች ( ዕድሜያቸው አስራ ሶስት ዓመት ያልሞላ) ላይ የሚፈፀም የግብረ ሥጋ ድፍረት በደል (አንቀጽ 627) ፣
ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ላይ የሚፈጸም የግብረሰዶም ጥቃትና ለክብረ-ንጽህና ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች (አንቀጽ 631)፣
- ለመልካም ሥነ ምግባርና ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆነ ብልግናና አሣፋሪ ሥራን በአደባባይ ለአካለመጠን ባልደረሰ ልጅ ፊት ሲፈፀም አንቀፅ 639/2
- ጸያፍ ወይም የብልግና ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ለሕዝብ መግለፅና፤ እንደዚህ ያሉትን ነገሮች ለአካለ መጠን ላልደረሱ ልጆች አስቦ ያሳየ፣ የሰጠ ወይም ያስረከበ (አንቀጽ 640 /2/ (ለ)) ወይም ለዚሁ ዓላማ አካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች የግብረስጋ ግንኙነት የፈፀሙ በማስመሰል ያሳየ ወይም ሀፍረተ ስጋቸው እንዲታይ ያደረገ (አንቀጽ 640 (ሐ)) እና
- ለአካለመጠን ያልደረሱ ልጆችን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ስራዎች የመጠበቅ ኃላፊነት ያለመወጣት (አንቀጽ 644)፣
- በሁለቱም ፆታ ላይ ሊፈፀም የሚችል ቢሆንም አንቀጽ 648 ላይ ያለዕድሜ ጋብቻ ብዙ ጊዜ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት መሆኑን እናስተውላለን።
- የሕፃን መወለድን ወይም ተጥሎ መገኘትን አለማስታወቅ (አንቀጽ 656)፣
- አስመስሎ ህፃንን ማቅረብ ወይም መለወጥ (አንቀጽ 657) ፣
- የቀለብ መስጠት ግዴታን አለመፈጸም (አንቀጽ 658 )፣
- የልጅ ማሳደግ ግዴታን አለመፈጸም (አንቀጽ 659 )
እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸው በኢፊድሪ ወንጀል ህግ ላይ የተደነገጉ ሲሆን ይህ ወንጀል ሲፈጸምባቸው በፈጻሚው ላይ ሊወሰድ የሚችል ቅጣት ፣ ወንጀል በመሆኑ ማህበረሰቡ አውቆ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ የሚያስገነዝብ ብሎም የህጻናትን አስተዳደግ ዋስትና የሚሰጥ ነው።

5. በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ- ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/12 አስመልክቶ የህጻናት መብት ጥበቃ...

በአዋጁ እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ሌላውን ሰው በባርነት ወይም በባርነት መሰል ተግባር፣ በአገልጋይነት ወይም ዕዳ መያዣነት የያዘው፣ አካሉን በማውጣት ወይም በዝሙት አዳሪነት ወይም መሰል የወሲብ ተግባር ብዝበዛ የፈፀመበት፣ በግዳጅ ስራ ወይም አገልግሎት፣ በልመና፣ በወንጀል ተግባር፣ በግዳጅ ጋብቻ ያሰማራ ወይም ሕፃናትን በጉልበት ስራ የበዘበዘ ወይም እነዚህን መሰል የብዝበዛ ተግባራት የፈፀመ እንደሆነ በሰው የመነገድ የወንጀል የፈፀመ እንደሆነ በሰዎች የመነገድ እና ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር አዋጅ 1178/12 አንቀፅ 3 መሠረት ይህ ያደረገው ሰው ይቀጣል።

በአዋጁ አንቀጽ 7 መሰረት ማንኛው ሰው ሌሎች ሰዎች ከሚፈጽሙት የዝሙት አዳሪነት ተግባር ወይም የሥነ-ምግባር ብለሹነት ለመጠቀም ሲል ወይም የሌላውን ሰው ፍትወተ ሥጋ ፍላጎት ለማርካት በማስብ ሌላውን ሰው ለዝሙት ተግባር ያሰማራ፣ ያገናኘ፣ ያቀረበ፣ በዝሙት አዳሪነት ያስቀመጠ፣ የሥራ ወይም የመኖሪያ ቤቱን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለዚህ ተግባር ያዋለ ወይም ያከራየ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ የሌላውን ሰው የዝሙት ድርጊት ወይም የሥነ-ምግባር ብልሹነት መጠቀሚያ አድረጎ መያዝ የሚያስቀጣ ነው።

በሌላ በኩል ማንኛውም ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንዲገባ፣ ከኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጣ፣ በኢትዮጵያ ግዛት እንዲተላለፍ ያደረገ ወይም ሰው ከኢትዮጵያ ግዛት ለማስወጣት ዝግጅት ያደረገ፣ በሂደት ላይ የተገኘ፣ ያጓጓዘ ወይም የተቀበለ እንደሆነ በዚህ አዋጅ መሠረት ይቀጣል።

6. የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የህጻናት መብት አስመልክቶ የሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም ...

6.1 በመዝገብ ቁጥር፡ 282248 አንድ ተከሳሽ ጥፋተኛ በተባለበት ድንጋጌ ላይ ቅጣቱ እንዳይገደብ በሕግ የተጣለ ግልጽ ክልከላ ከሌለ በስተቀር፤ ተከሳሹ የሚያስተዳድራቸው ሕፃናት ልጆች ካሉት ፍርድ ቤቶች ቅጣቱን ሊገድቡ እንደሚገባ ተወስኗል።
6.2 ስለ ቀለብ አስመልክቶ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መ/ቁ 98552 የፌደራል የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 197 እና 202 መሠረት በማድረግ ስለ ህጻናት ቀለብ የተሰጠ የህግ ትርጉም የህጻናትን ቀለብ የማግኘት መብት የሚደግፍ ነው።

7. የህግ እና የአፈጻጸም ክፍተቶች

7.1 ከጥቂት ወንጀሎች በቀር በህጻናትም ሆነ በአዋቂ ላይ በሚፈጸሙ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው የቅጣት እርምጃዎች ተመሳሳይ መሆናቸው

7.2 የወንጀል ክትትል ድክመት
በህጻናት ላይ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በቤት ውስጥ ተደብቀው መቅረታቸው ለዚህም በቤት ሊፈጸሙ የሚችሉ ወንጀሎችን ሊከታተል የሚያስችል አስተማማኝ ክትትል አለመኖሩ

7.3 የግንዛቤ ማነስ

ማህበረሰቡ ከዚህ አንጻር ባለበት ቦታ ሆኖ በቂ የሆነ የህግ ግንዛቤ እንዲደርሰው የማድረግ ችግር
ጥቂቶቹ ሲሆኑ ጥናት በማድረግ ሌሎችንም ጭምር በመለየት መፍትሄ ሊበጅላቸው ያስፈልጋል።

8. የህግ ምክር

ህጻናት ከአለምአቀፍ ህጻናት ኮንቬሽንም ሆነ በሌሎች ህግጋት አንጻር እንክብካቤና ልዩ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ከጥቅማቸው አንጻር ከፍ ያለ የህግ ከለላ ያሻቸዋል። ከዚህም አንጻር ያለውን መብቶቻቸውን በተመለከተ ማህበረሰቡም ሆነ ህጻናቱ እንዲያውቀው በማድረግ መብታቸው እንዲጠበቅ እንዲሁም ባለው ክፍተት ላይ ጥናት በማድረግ የተሻለ የህግ ጥበቃ እንዲኖር ማድረግ የማህበረቡ፣የህግ አውጪው በተለየም የፍትህ አካላቱ ድርሻ ነው።

ማጣቀሻዎች
1. የኢፊድሪ ህገመንግስት ፥ አዋጅ ቁጥር 1/1987
2. የፍ/ር ህግ አዋጅ ቁጥር 165/1952
3. የኢፊድሪ ወንጀል ህግ 1996
4. የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ 213/1992
5. የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የህግ ትርጉም የተሰጠባቸው መ/ቁ 282248 እና 98552
6. በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ- ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/12
7. የፍትህ ሚኒስትር የፌስቡክ ገጽ

https://t.me/Fantahunlawye...
https://www.facebook.com

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.