Logo
YenetaTube
የቀድሞው የሊቢያ መሪ የኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ ልጅ የሆነው ሰይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ መገደሉ ተዘገበ።

የ53 ዓመቱ ሰይፍ አል-ኢስላም በአንድ ወቅት የአባቱ አልጋ ወራሽ ተደርጎ ይታይ የነበረ ሰው ነው።

የሊቢያ የዜና ወኪል እንደዘገበው የሰይፍ አል-ኢስላም የፖለቲካ ቡድን መሪ ግድያውን አረጋግጠዋል። ጠበቃው ለኤ.ኤፍ.ፒ እንደተናገሩት በዚንታን ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ "አራት አባላት ያሉት የኮማንዶ ቡድን" ግድያውን ፈጽሞበታል። ጥቃቱን ማን እንደፈጸመው ግን እስካሁን ግልጽ አልሆነም። በሌላ በኩል ደግሞ እህቱ ለሊቢያ ቴሌቪዥን እንደተናገረችው ሰይፍ አል-ኢስላም የሞተው በሊቢያ እና አልጄሪያ ድንበር አቅራቢያ ነው።

ሰይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ እ.አ.አ ከ1969 ጀምሮ ሊቢያን በመሩትና በ2011 በሕዝባዊ አመፅ ተወግደው በተገደሉት በአባቱ ሙአመር ጋዳፊ ዘመን ከእሳቸው ቀጥሎ በሀገሪቱ እጅግ ተደማጭነት ያለውና የሚፈራ ሰው ነበር።

በ1972 የተወለደው ሰይፍ አል-ኢስላም እ.ኤ.አ ከ2000 ጀምሮ የጋዳፊ አገዛዝ እስከተገረሰሰበት ጊዜ ድረስ ሊቢያ ከምዕራባውያን ጋር የነበራትን ግንኙነት በማደስ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

ምንም እንኳን በመንግሥት ውስጥ ይፋዊ ሥልጣን ባይኖረውም አባቱ በስልጣን ዘመናቸው የኒውክሌር መሣሪያ ፕሮግራማቸውን እንዲያቋርጡ ያደርጓቸው የነበሩትን ከፍተኛ ድርድሮችን በቀዳሚነት መርቷል። በዚህም በሊቢያ ላይ ተጥለው የነበሩ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች እንዲነሱ ምክንያት ሆኗል።

ሰይፍ አል-ኢስላም በ2011 የፀረ-መንግሥት ተቃውሞዎችን በጭካኔ በማፈን ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና ነበረው በሚል ተከሷል። የአባቱ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ በዚንታን ከተማ በሚገኝ ተቀናቃኝ ሚሊሻ እጅ ወድቆ ለስድስት ዓመታት ያህል ታስሮ ቆይቷል። የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል በሚልም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ይፈለግ ነበር።

በ2015 ደግሞ በሊቢያ መዲና ትሪፖሊ በሚገኝ ፍርድ ቤት በሌለበት የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ነበር። ይሁንና በምስራቅ ሊቢያ (ቶብሩክ) በሚገኝ ሚሊሻ አማካኝነት በ2017 በምህረት አዋጅ ከእስር ተለቆ ነበር።

ሰይፍ አል-ኢስላም ምንም እንኳን ቀደም ሲል "ሥልጣን እንደ እርሻ የሚወረስ አይደለም" በማለት የአባቱን ቦታ ለመረከብ እንደማይፈልግ ቢገልጽም በ2021 ግን ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደር አስታውቆ ነበር። ሆኖም ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ በመራዘሙ ፍላጎቱ ሳይሳካለት ቀርቷል።

Ethio Fm

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.