Logo
FastMereja
የፊልም ባለሙያ ቴዎድሮስ ተሾመ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ግልጽ ደብዳቤ ላከ

​#fastmereja I ታዋቂው የፊልም ባለሙያ ቴዎድሮስ ተሾመ፣ በአባይ ወንዝ እና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን የኢትዮጵያን ጽኑ አቋም የሚገልጽና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጉዳዩን እውነታ እንዲረዱ የሚያሳስብ ግልጽ ደብዳቤ አሰራጨ።

​ቴዎድሮስ "ፕሬዝዳንት እውነታውን ይረዳ ዘንድ ሼር አድርጉት" በሚል መሪ ቃል ባቀረበው በዚህ በእንግሊዘኛ በቀረበ ደብዳቤ፣ አባይ ከኢትዮጵያ ምድር የሚመነጭ የተፈጥሮ፣ የጂኦሎጂ እና የፈጣሪ ስጦታ እንጂ በማንኛውም ስምምነት ወይንም በግዛት ትዕዛዝ የተፈጠረ አለመሆኑን በአጽንኦት ገልጿል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት የመጠቀም መብት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የተፈጠረ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ህጎች (ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም) የታወቀ መሆኑን ጠቁሟል። ግድቡ ውሃውን እንደማይገታውና ለዜጎች ብርሃን ለመስጠት ብቻ የሚውል የልማት ስራ እንጂ የጥቃት እርምጃ አለመሆኑን አስገንዝቧል።

​ግብፅ ለዘመናት አባይን የራሷ ብቻ አድርጋ የምትቆጥርበት የ1929 እና የ1959 ውሎች፣ ኢትዮጵያ ያልፈረመችባቸውና በቅኝ ገዥዎች የተፈረሙ በመሆናቸው በኢትዮጵያ ላይ ምንም አይነት ተፈጻሚነት እንደሌላቸው በደብዳቤው ተብራርቷል።

​ግብፅ ኢትዮጵያን ደካማና የባህር በር አልባ አድርጎ ለማስቀረት በታሪካዊ ጠላቶቻችን በኩል ስታደርግ የነበረውን ሴራ ቴዎድሮስ አስታውሷል። በተለይም በደርግ ዘመን ማብቂያ ላይ ግብፅ ኤርትራን በመርዳት ኢትዮጵያ የዓሳብ ወደብን እንድታጣ ያደረገችው ተንኮል ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የማይረሳ ቁስል መሆኑን ገልጿል።

​የአባይ ጉዳይ የጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት ማሟያ መሆን እንደሌለበት የገለጸው ደብዳቤው፣ ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ ሊፈታ የሚገባው "የወንድማማቾች ጉዳይ" መሆኑን ለፕሬዝዳንቱ አሳውቋል።

​ቴዎድሮስ ተሾመ ደብዳቤውን ሲያጠቃልል "ፍትህ እንደ አባይ ፈሳሽ የጸና፣ ሉዓላዊነትም እንደ ኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች የማይናወጥ ይሁን" ብሏል። ኢትዮጵያ የግብፅን መራብም ሆነ የሱዳንን መጨለም እንደማትመኝ፣ ነገር ግን የገዛ ቤቷን ለማብራት ያላትን መብት ለማንም እንደማትተው በማሳሰብ መልዕክቱን አጠቃሏል።

7 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.