Logo
Getu Temesgen
የአብዛኛውን ሰው ትኩረት ፍለጋ (Public Validation)የማህበረሰብ ስነልቦና መዛነፍ እና ግልብነትን ማስፋፋት...

(የሀብታሙ ደባሱ አዲሱ ሀሳብ)
#ethiopia | ዛሬ በተለየ እይታ ነገረ -ሀሳቤን ለማቅረብ እወዳለሁ በዘመናችን ያለው ፈጣን የቴክኖሎጂ እና የማኅበራዊ መስተጋብር ለውጥ ወጣቱ ትውልድ ትኩረት የሚፈልግባቸውን እና ማንነቱን የሚመዝንባቸውን መመዘኛዎች እየቀየረ ነው።

"የአብዛኛውን ሰው ትኩረት ፍለጋ" (Public Validation) ተብሎ የሚጠራው ይህ ክስተት፣ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ (Social Media) መድረኮች በሚፈጠረው ተጽዕኖ፣ የአብዛኛው ወጣት ስነልቦናዊ መሠረት እየሆነ መጥቷል።

ይሁንና፣ይህ ፍለጋ ከግል ማንነት ምስረታ አልፎ፣ የማኅበረሰብ ስነልቦናዊ መዛነፍ እና አዋቂና ብልሆችን የመዘንጋት ተለምዷዊ ክስተት እንዲከሰት ምክንያት እየሆነ ነው።በዚህም ወጣቶች ለነገ መሰረታቸው የእውቀት ምንጭ የሆኑ ሥራዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ ቅቡልነት ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት እርቃንን ወደ አደባባይ እስከ ማቅርብ ደርሷል ።

ይህን ማህበረሰባዊ ህመም በጊዜ ካላከምነው የመረጃ መተራመስ (Information disorder ) ሊያስከትለው የሚችለው በህፃናት ፣በታዳጊዎች እና በወጣቶች ህይወት ላይ ከፍተኛ ፈተና ነው ። እስኪ ነገሩ በአስታውሎት እንመልከተው :-

🔴 የአብዛኛውን ሰው ትኩረት ፍለጋ (Public Validation) እና የወጣቶች ፈተና:- ዛሬ የወጣቶች የትኩረት ማዕከል ከቤተሰብ እና ከአካባቢው እውነታ ወደ ዲጂታል መድረኮች ተቀይሯል። የ'ላይኮች' (Likes)፣ 'አስተያየቶች' (Comments) እና 'ተከታዮች' (Followers) ቁጥር የግለሰቡን ክብደት፣ ተቀባይነት እና ዋጋ የሚለካበት ዋና መመዘኛ እየሆነ መጥቷል። ማኅበራዊ ሚዲያ ለሚያቀርበው ነገር ፈጣን ምላሽ (ትኩረት) ማግኘት ወጣቶች ከረጅም ጊዜ ልፋትና ትዕግስት ይልቅ ፈጣንና ጊዜያዊ እርካታን እንዲመርጡ ያደርጋል። ( ትምህርት እና ንባብ ሰፊ የአንጎል ሥራ የሚጠይቁ ትግባራትን መሸሽ )

🔴የማይጨበጥ ምስል (Unrealistic self image ):-ወጣቶች ሌሎች ከፍ አድርገው የሚመለከቱትን 'ምርጥ' ማንነታቸውን ለመፍጠርና ለማሳየት ይገደዳሉ።ይህም በውስጣቸው ባለው እውነተኛ ማንነት እና በሚያሳዩት የውጭ ምስል መካከል የስነልቦና ክፍተት እንዲፈጠር ያደርጋል። (ሌላን ሰው ለመምሰል የሚደረግ ጥረት) ከመጠን ያለፈ ውድድር ትኩረት ለማግኘት የሚደረገው ዘለቄታ የሌለው ውድድር ለጭንቀት (Anxiety)፣ ለድብርት (Depression) እና ከማኅበረሰቡ የመገለል ስሜት (Social Isolation) እንዲጨምር ያደርጋል። (ትናንት በተካሄደው የቲክቶክ ሽልማት ያልተሸለሙ ተሳታፊዎች እንደተመለከትኩት ጭንቀት ውስጥ የገቡ ይመስላል )

🔴የማኅበረሰብ ስነልቦናዊ መዛነፍ፦
የአብዛኛውን ሰው ትኩረት ፍለጋ የግለሰቡን ስነልቦና ብቻ ሳይሆን መላውን ማኅበረሰብ የሚነካ መዛነፍ ያስከትላል።የእውነት እና የውሸት መደበላለቅ በሰፊው የብዙኃን ትኩረት የተሰጠው ሐሳብ ወይም መረጃ፣ ትክክለኛነቱ ሳይረጋገጥ በቀላሉ "እውነት" ተብሎ የመወሰድ አዝማሚያ ይጨምራል። የጥራት (Quality) ደረጃ ከብዛት (Quantity) በታች ይሆናል።

🔴የጥልቅ ውይይት መጥፋት:፦ውስብስብ እና ጥልቅ የሆኑ ጉዳዮች በትዊተር (Twitter) ወይም በቲክቶክ (TikTok) በፈጣን ቅብብሎሽ ውስጥ ሲቀርቡ፣ በወጉ የመተንተንና የመወያየት ዕድል ይዘጋል።ጥልቀት የሌለው የገጽታ ግንዛቤ (Superficial Understanding) ይስፋፋል።

🔴የጋራ እሴቶች መናድማኅበራዊ ትኩረት በጊዜያዊ ፋሽን (Trend) እና ስሜታዊ ይዘቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ለዘመናት የቆዩ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና የሞራል እሴቶች ቦታ ያጣሉ፤ ነውር የሚባል ነገር እየቀረ ድንቁርና በአደባባይ ቦታ ያገኛል ።

🔴 አዋቂና ብልሆችን የመዘንጋት ተለምዷዊ ክስተት እና ግልብነትን ማስፋፋት ፦ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የተነሳ፣ ወጣቱ ትውልድ ለረጅም ጊዜ በሕይወትና በእውቀት ልምምድ ያካበቱትን አዋቂዎችንና ብልሆችን ምክርና ተሞክሮ ዋጋ የመንሳት እና የመዘንጋት አዝማሚያ እየተስተዋለ ነው።የትውልድ ክፍተት (Generational Gap) መስፋት ፈጣን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለውጦች ወጣቶችን በአዲስ "ቋንቋ" እና "እሴት" እንዲመሩ ያደርጋቸዋል።ይህ ደግሞ ከአዋቂዎች ጋር ያላቸውን የመግባቢያ ድልድይ ያፈርሳል።ሙያዊ የዩኒቨርስቲ እውቀት በሊቃውንት የተመሰከረ ጠልቅ እውቀት እየተረሳ የጨረባ የስብዕና ግንባታ እንደ አዎቂነት እየተወሰደ ነው ።

✍️ እንደ መውጫ⁉️

በመጨረሻም፣ የአብዛኛውን ሰው ትኩረት ፍለጋ የወጣቶችን የጊዜያዊ እርካታ ፍላጎት ሊያረካ ቢችልም፣የዘላቂነት ጥበብን እና ጥልቅ የማኅበረሰብ ትስስርን የሚያሳጣ አደገኛ መንገድ ነው። ሁላችንም እውነተኛ እሴት የሚገኘው ከውስጣዊ ማንነት እና ከተከማቸ የጥበብ ምንጭ እንጂ፣ ከዲጂታል ምላሾች ብዛት አለመሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል።ይህንም ለልጆቻችን ምን እንደምናስተምራቸው ቆም ብለን ማሰብ ወይም የማህበረሰብ ንግግር ( community conversation ) የሚስፈልግ ይመስለኛል ።

Ethiopia 🇪🇹

ለበለጠ ወዳጅነት የፃሃፊውን የኤክስ(X) እና የፌስቡክ ገፅ ይከታተሉ :-

🔗የኤክስ(X)ገፅ:-https://x.com/HDebasu?t=eR...

🔗የፌስቡክ:-https://www.facebook.com/s...

መልካም እሁድ 🙏

8 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.