Logo
Getu Temesgen
ኢሊዩድ ኪፕቾጌ፦

"አንታርቲካ ላይ መሮጥ እፈልጋለሁ"

(ምስጋናው ታደሰ)
#ethiopia | አንጋፋው አትሌት ኢሊዩድ ኪፕቾጌ ከታላላቅ የማራቶን ውድድሮች ራሱን ማግለሉን አስታወቀ። በ40 ዓመቱ ትናንት በተካሄደው የኒውዮርክ ማራቶን ተሳትፎ 17ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኬንያዊው ፊቱን ከትራክ ወደ ማራቶን ካዞረ በኋላ የቀረው ብቸኛ ውድድር የኒውዮርክ ማራቶን እንደነበርና እሱን በማሳካቱም ደስተኛ መሆኑን ገልጿል።

"ማራቶንን የማቆመው አርጅቼ አይደለም" ያለው አንጋፋው አትሌት "ሁልጊዜም ወደ ውድድር የምገባው ለመሳተፍ ሳይሆን ለማሸነፍ ነው። የሽልማት መድረኩ ላይ መቆም እፈልጋለሁ። አሁን ባለው ተጨባጭ ዕውነታ ደግሞ ውድድሮችን ጀምሮ ለመጨረስ የሚያስችል እንጂ የሽልማት መድረኩ ላይ ለመቆም የሚያስችል ጉልበት አለኝ ወይ? አይመስለኝም። ስለዚህ በክብር ማቆሙ ይሻላል። ጥንካሬዬ ግን አሁንም አብሮኝ እንዳለ ነው። ሌላው ቀርቶ በሳውዲ አረቢያ ሙቀት ውስጥ እንኳን 50 ኪሎሜትር ሮጦ ለመጨረስ የሚያስችል አቅም አለኝ" ብሏል።

ኪፕቾጌ "World Marathon Majors" ተብለው ከሚጠሩት መድረኮች ራሱን ቢያገልም በተለያዩ ቀለል ያሉ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ በወጣቶች ዘንድ መነቃቃትን እንደሚፈጥርም ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም ቀጣይ ህልሙን አስመልክቶ ሲጠየቅም "ያልተሞከሩ ነገሮችን በመሞከር ለአዲሱ ትውልድ ጥሩ ምሳሌ ለመሆን እፈልጋለሁ። ስለዚህ ከተሳካልኝ አንታርቲካ ላይ መሮጥ እፈልጋለሁ" ሲል በሳቅ ታጅቦ መልሷል።

ኢሊዩድ ኪፕቾጌ በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ ደረጃ በተሰጣቸው ሰባቱ ዋና ዋና ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች (በርሊን፣ ለንደን፣ ቦስተን፣ ቶኪዮ፣ ሲድኒ፣ ቺካጎ እና ኒውዮርክ) ላይ በሙሉ በመሳተፍና በማሸነፍ ብቸኛው አትሌት ሆኗል። ለዚህ ክብሩም ከትናንቱ የኒውዮርክ ማራቶን በኋላ ባለ ሰባት ኮከብ አትሌትነቱን የሚያረጋግጥ የክብር ሜዳልያ ተሸልሟል። እሱም በእንባ ታጅቦ ስንብቱን ይፋ አድርጓል።

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.