Logo
Getu Temesgen
ልጆቻችሁን እዩዋቸው! ችግራቸውን ተረዷቸው!!

ልጆቻችሁ መጻፍ አይሆንላቸውም? ...ማንበብስ? ...ሂሳብ ማስላት ላይስ እንዴት ናቸው? ....ትምህርትስ አይገባቸውም?

መቼም ብዙዎቻችሁ ስለኦቲዝም ስታስቡ የምታስቡት ነገር ተመሳሳይ ነው፡፡ አንድ ልጅ ፊቱ ላይ ከሌሎች ልጆች የተለየ አይነት መልክ ሲኖረው፣ ከንፈሩን መግጠምና ምላሱን መሰብሰብ አዳግቶት የአፉን ፈሳሽ መቆጣጠር ሳይችል ሲቀር ፣ ወይም ራሱን የሚመታ ወይም ሰው የሚተናኮል ሲሆን ወዘተ ነው እናንተ ኦቲዝም ያለበት የሚመስላችሁ አይደል?

ትልቅ ስህተት ነው፡፡

እንዲህ ያሉ ምልክቶች ብዙ ጊዜ 'ዳውን ሲንድረም' የሚባለው አይነት የዐዕምሮ እድገት መዘግየት ችግር ባለባቸው ልጆች ላይ የሚከሰት ነው፡፡ እሱን ሌላ ጊዜ እናወራዋለን፡፡

ኦቲዝም ግን ምንም በአይን ታይቶ የሚታወቅ መልክ የለውም፡፡ አንድን ህጻን አይታችሁ ኦቲዝም እንዳለበት መበየን በፍጹም አትችሉም፡፡ ኦቲዝም ምንም አይነት የፊት ቅርጽ መለየት ወይም የአካል አፈጣጠር ልዩነት አይስተዋልበትም፡፡ እንደውም ብዙ ጊዜ ብዙዎችን በሚያስገርም ሁኔታ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች በጣም ቆንጆዎችና መልከቀናዎች ናቸው፡፡

ኦቲዝም ብዙ መገለጫዎች አሉት፡፡ አሁን ስለኦቲዝም ሳይሆን ከኦቲዝም ጋር ተመሳሳይ በሆነ የዐዕምሮ ዕድገት ስርዓት መዛባት ሳቢያ የሚፈጠሩ ችግሮችን ላወራችሁ ነው፡፡

የማንበብ ክህሎትን ማጣት፣ የመጻፍ ክህሎትን ማጣት እና ሂሳብ የማስላት ክህሎትን ማጣት የሚባሉ ችግሮች አሉ፡፡

"ሂሳብ የማስላት ክህሎትን ማጣት " ከዐዕምሮ ዕድገት ስርዓት መዛባት ኹኔታዎች (Neurodevelopmental disorder conditions) ውስጥ የሚካተተው የትምህርት ክህሎት ማጣት (Learning disability) ችግር አንዱ መገለጫ ነው፡፡

Learning disability ከምንላቸው የመማር ክህሎትን የማጣት ችግሮች ውስጥ የሚመደበው ሂሳብ የማስላት ችግር በሳይንሳዊ አጠራሩ Dyscalculia ተብሎ ይጠራል፡፡ አንድ ተማሪ ህጻን ቀላልና ማንም ሊሰራቸው የሚችል የሂሳብ ስሌቶችን ለመስራት ሲያዳግተውና በአጠቃላይ ስሌት አልገባ ሲለው Dyscalculia ሊኖርበት እንደሚችል መጠርጠርና ለባለሙያ ማሳየት አይከፋም፡፡

ማንበብ እየቻሉ እርሳስ ወይም ስክሪፕቶ ይዘው መጻፍ በፍጹም የማይሆንላቸው ልጆች ደግሞ አሉ፡፡ "መጻፍ አይወዱም፣ ይቸከችካሉ" እየተባሉ ለቅጣት ይዳረጋሉ፡፡ ስክሪፕቶና እርሳስ አጥብቀው መያዝም ሆነ በአግባቡ መስመር ተከትለው መጻፍ አይሆንላቸውም፡፡ ፈልገው አይደለም፡፡ ይህ ችግር Dysgraphia ይባላል፡፡ ብዙ ልጆች ጎበዝ ተማሪዎች ሆነው ሳለ መጻፍ ግን 'ሞታቸው' ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ችግራቸውን የሚረዳላቸው ስለሚያጡ ለቅጣትና ለቁጣ ይዳረጋሉ፡፡ እንዲህ አይነት ልጆች ካሏችሁም ለባለሙያ አሳዩዋቸው፡፡

የትምህርት ክህሎት ማጣት ችግር ሌላው መገለጫ ደግሞ "የማንበብ ክህሎትን ማጣት " ወይም በህክምና ቋንቋ Dyslexia የሚባለው ነው፡፡ ይህ ችግር ያለባቸው ልጆች መጻፍ ቢችሉም ማንበብ ግን አይችሉም፡፡ ፊደሎቹ አይናቸው ስር ስለሚንቀሳቀሱባቸው ተረጋግተው አይታዩዋቸውም፡፡ በዚህ ሳቢያ ዐዕምሯቸው ይረበሻል፡፡ እንዲህ አይነት ልጆችም በተመሳሳይ ትምህርት ቤት ገብተው ማንበብ ስለማይሆንላቸው ለቅጣት እና ለቁጣ ይዳረጋሉ፡፡ ችግራቸውን የሚረዳላቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡

በአጠቃላይ "ልጄ ትምህርት አይገባውም፣ ትምህርት አይወድም፣ ሰነፍ ነው፣ ደደብ ነው" ወዘተ እያሉ ልጆችን መቅጣትና በልጆች ላይ መጮህ ትርጉም ያለው ውጤት አያመጣም፡፡ የገለጽኩላችሁ ነገር ሁሉ በቴራፒ መስተካከል የሚችል ነገር ስለሆነ ለባለሙያ ማሳየትና ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ሳይንሳዊ ቴራፒ ድጋፍ ማድረግ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡

ኦቲዝም (ASD) ፣ የመረጋጋትና የትኩረት ማጣት (ADHD) ፣ ወይም የትምህርት ክህሎት ማጣት ( learning Disability) በተመሳሳይ የዐዕምሮ ዕድገት ስርዓት መዛባት (Neuro developmental disorder) ምክንያት የሚመጡ ችግሮች ናቸው፡፡ ሶስቱም የመሻሻል ተስፋ ያላቸው በመሆናቸው ባለሙያ ማማከር እንጂ "ልጄ ይህ ችግር የለበትም" ብሎ ለመቀበል አለመፈለግ ወይም መደበቅ ማንንም አይጠቅምም፡፡

የልጆቻችሁን ችግር ሳታውቁ ዳተኛ አድርጋችሁ አትፈርጇቸው፡፡ ተረዷቸውና አግዟቸው፡፡

መላኩ ብርሃኑ
የኦቲዝም መብቶች ተሟጋችና የበጎ ፍቃድ አምባሳደር

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.