Logo
FIDEL POST NEWS
ጥቅምት 6 2018

የግዕዝ ቋንቋ በአማራ ክልል በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መሰጠት በዚህ ዓመት ተጀምሯል፡፡

ይህንን ተከትሎ ጉዳዩ መነጋገሪያ ወጥቶታል፡፡

አንዳንዶች እስይ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ አስፈላጊ አይደለም ልጆቻችንም አይማሩም ሲሉ ተሰምተዋል፡፡

ቀሪዎቹ ደግሞ በቋንቋ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ ባያነሱም ከስንተኛ ከፍል ጀምሮ ነው ቋንቋው ለተማሪዎች መሰጠት ያለበት በሚለው ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡

“የግዕዝ ቋንቋ በትምህርት ስርዓት ውስጥ” በሚል ርዕስ ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም  በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት በርካታ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተሳታፊዎች በተገኙበት ውይይት ተካሄዷል፡፡

በስነ ልሳን መምህሩ እና ተመራማሪው ዘላለም ልየው(ፕ/ሮ) አወያይነት፤ በበድሉ ዋቅጅራ(ዶ/ር) እና በይኩኖአምላክ መዝገቡ መካከል ውይይት ተደርጓል፡፡

የግዕዝ ቋንቋ በትምህርት ስርዓት ውስጥ ስላለው አስፈላጊነት እና ከስንትኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጥ በሚለው ጉዳይ ላይ ተወያዮቹ የየራሳቸውን ሃሳብ ሰንዝረዋል፤ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችም  መልስ  ሰጥተዋል፡፡

በግዕዝ ቋንቋ አስፈላጊነት ላይ በስነ ልሳን መምህሩ በድሉ ዋቅጅራ(ዶ/ር) እና በግዕዝ ቋንቋ ተመራማሪው አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ መካከል ልዩነት የለም፡፡ ለስነ ጽሁፍ፣ ለስነ ከዋክብት፣ ለግብርና፣ ለባህላዊ ህክምና፣ታሪክን ለመረዳት እና ለምርምር  አገልግሎት ቋንቋው ባለው አቅም ይስማማሉ።

የግዕዝ ቋንቋ በትምህር ስረዓት ወስጥ ተካትቶ ከስንተኛ ከፍል ጀምሮ ይሰጥ በሚለው ግን ይለያያሉ።

በድሉ ዋቅጅራ(ዶ/ር) ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ቢሰጥ ሲሉ አቶ ይኩኖአምላክ በበኩላቸው ተማሪዎች በደንብ ቋንቋዉን እንዲይዙት ከ4ኛ እስክ 8ኛ ክፍል ቢሰጥ እና ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ በምርጫ እና በፍላጎት ቢሆን ሲሉ ሃሳባቸው አጋርተዋል።

በድሉ ዋቅጅራ(ዶ/ር) የግዕዝ ቋንቋ አሁን የሃይማኖት ቋንቋ ብቻ መሆኑ አስረድተው፤ አንድ ቋንቋ በስነ ልሳን ሞቷል የሚባለው ምን ሲሆን ነው? የሚለውን ሲያብራሩ አንድ ቋንቋ ተናጋሪው ከ25,000 በታች ሲሆን አደጋ ውስጥ ያለ ቋንቋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአፍ መፍቻ ተናጋሪ ማህበረሰብ ሲያጣ ደግሞ ሞቷል እንደሚባል በለሙያው ጠቁመዋል፡፡

በድሉ ዋቅጅራ(ዶ/ር) የግዕዝ ቋንቋ ላይ የሚሰራ ኮሚቴ ወይም ማህበር አቋቁሞ የመናገሪያ ቋንቋ እናደርገዋለን ማለት አንደሚከብድ ተናግረው ምክንያቱ ደግሞ ተናጋሪው ማህበረሰብ በሌላ ቋንቋ መናገር ስለጀመረ መልሶ መናገሪያ ማድረግ አስቸጋሪ ነው ብለዋል።

"አንድ ቋንቋ ሞቷል ማለት ልክ እንደ አማርኛ እና ኦሮምኛ የሚናገረው ማህበረሰብ የለውም ማለት ነው" የሚሉት በድሉ ዋቅጅራ ነገር ግን ሁለተኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሉትም ማለት አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።

ላቲን፣ ግሪክን እና ግዕዝን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ የሚናገሯቸው እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

ለምሳሌ ግዕዝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ እንደሚውል ያስረዱት በድሉ(ዶ/ር) ለመናገሪያ ባይውልም ለስነ ከዋክብት ጥናት፣ ለስን ጽሁፍ፣ ታሪክን ለመረዳት ይረዳል ሲሉ አብራርተዋል።

አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ በበኩላቸው የስነ ልሳን ባለሞያዎች ቋንቋን ሞቷል ወይም አልሞተም በለው ለመበየን የሚጠቀሙት ስነ ልሳን የተማሩበትን የውጪውን አለም ሳይንስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እኛ የራሳችንን  መመዘኛ መቀረጽ እንችላለን ብዬ አስባለው ሲሉ አስረድተዋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ሞትን በተለያየ ደረጃ የሚበይን አንድ ብሔረሰብ እንዳለ ሰምቻለው አልያም አንብቤያለሁ። አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ከስጋው ስትለይ ነው እኛ ሞተ የምንለው፤ ነገር ግን እነሱ ሞተ አይሉም ምክንያቱም ልጆቹ፣ ሚስቱ እና ቤተሰቡ ሁሉ ስላሉ ብለው አስረድተዋል።

ስለዚህ ሞተ ሳይሆን ሌላ ቃል አላቸው መቃብሩም የሚሰራው ያን ታሳቢ ያደረገ ነው። ሀገር ሙሉ እያወቀው እንዴት ሞቷል ይባላል። ከዚያ እሱ የሚያውቃቸው የእድሜ እኩዮቹ በመላ ሲያልፉ ወደ ሞት ትንሽ ጠጋ ይላል፣ ሌሎች ያልፋሉ አሁንም ወደ ሞት ጠጋ ይላል ከዚያ ልጆቹ አልፈው ከሰው ትዝታ ጨርሶ ሲፋቅ ነው ሞተ የሚባለው ሲሉ አስረድተዋል።

አሁን ግዕዝ እንዳለመታደል ሆኖ በምሁራን አካባቢ ነው የማይታውቀው እንጂ ብዙ ሰው ያውቀዋል። ስለዚህ የሞቱን ጉዳይ በዚያ ብንዳኛው፤ እኛ የራሳችንን መመዘኛ ብንይዝ ብለዋል አቶ ይኩኖአምላክ። ግዕዝ ከቋንቋዎቻችን አንዱ ነው ያሉት አቶ ይኩኖአምላክ ለዕለት ተዕለት አንነጋገርበትም፣ ለወደፊትም እንነጋገርበት በሚለውም እኔ አልስማማም ምክንያቱም አማርኛም ራሱ እራሱን ችሎ እየተነገረ ስላልሆነ ብለዋል።

ግዕዝ የንግግር ቋንቋ የማይሆነው ባለቤት ስለሌለው ሳይሆን ከንግግር ከወጣ ረዥም ጊዜ ስለሆ ነው አሁን እሱን ለመተካት የምንጨምራችው ቃላት ሌላ ቋንቋ ነው የሚያደርጉት አስፈላጊም አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።
ሸገር ራዲዮ
10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.