Logo
FastMereja
የሜሮን ጌትነት "ሌላ ዕውነት የለኝም" ታተመ
(ከዕዝራ እጅጉ)

ከ80 በላይ ግጥሞችን የያዘውና 134 ገፆች ያሉት "ሌላ ዕውነት የለኝም" የተሰኘው የሜሮን ጌትነት መፅሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው።

ሜሮን በተለያየ ጊዜ የጻፈቻቸውን ግጥሞች በአንድ ላይ አድርጋ ለሕትመት ያበቃች ሲሆን ግጥሞቹም በግላዊ ገጠመኝና ዕይታ ላይ ትኩረታቸውን ያደርጋሉ።

ለ 10 ዓመታት መኖሪያዋን ባህር ማዶ አድርጋ የነበረችው የኪነ- ጥበብ ሰው ሜሮን ጌትነት ለጥቂት ዓመታት ከጥበቡ ዓለም ራቅ ብላ መቆየቷ ይታወቃል።

ለሥነ- ግጥም ልዩ አክብሮት አለኝ የምትለው ሜሮን በአዲሱ መፅሐፏ የሚሰማትን ገልጻለች።

"ሌላ እውነት የለኝም በተለያየ ጊዜ፣ ቦታ እና ሁኔታ ውስጥ ሆኜ የፃፍኳቸው ግጥሞች ስብስብ ነው። ግላዊ ስሜቶች፣ እውነቶችና በህይወት መስመር ላይ ያስተዋልኳቸው ማህበራዊ ሁነቶች ከጫሩብኝ ሀሳቦች ተነስቼ የከተብኳቸው ናቸው ትወዷቸዋላችሁ።"ስትል ሜሮን ሀሣቧን ለተወዳጅ ሚድያ ትገልጻለች።

ሜሮን ጌትነት፣ የህይወት ታሪኳ በአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ መዝገበ አእምሮ ላይ የተሰነደ ሲሆን ከግጥም ባሻገርም ቴአትር ፍቅር አላት።

ሜሮን ጌትነት በምሥራቅ ሀረርጌ አሰበ ተፈሪ /ጭሮ/ ከተማ ሰኔ 10 ቀን 1975 ዓ.ም የተወለደች ሲሆን በወላጆችዋ የሥራ ዝውውር ምክንያት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በተለያዩ የሃገሪቷ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውራ የተማረች ሲሆን ይህም 1ኛ ክፍልን ወለጋ ሻምቡ አንደኛ ደረጃ፤ 2ኛ እና 3ኛ ክፍልን በአዲስ አበባ ህብረት በልጅነት፤ 4ኛ ክፍል በአራት ኪሎ ቅድስት ስላሴ፤ 5 ኛ ክፍልን በጠመንጃ ያዥ፤ 6ኛ ክፍል በአሰበ ተፈሪ ቁጥር አንድ፣ 7ኛ እና 8ኛ ክፍል በእውቀት ፋና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በአብዮት ቅርስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቃለች።

ከዚያም በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በማርኬቲንግ ክፍል በዲፕሎማ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል በዲግሪ የተመረቀች ሲሆን የሁለተኛ ዲግሪዋንም በዚሁ ትምህርት ክፍል በቴአትር ለልማት /Theatre for Development/ ተከታትላለች።

ይህ በተለያዩ አካባቢዎች የማደግና የመማር አጋጣሚ ከሰዎች ጋር በቶሎ የመግባባትና ወዳጅነት የመፍጠር እንዲሁም ከአካባቢና ሁኔታዎች ጋር በፍጥነት መላመድ እንድትችል ያገዛት ሲሆን ለኪነጥበባዊ ምልከታዎቿና ለፈጠራ ዝንባሌዋ መሰረት ሆኗታል።

የኪነጥበበ ጉዞዋን የጀመረችው ሜሮን የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ በነበረችበት ወቅት በጋሽ አበራ ሞላ የወጣቶች ፕሮጀክት አማካኝነት የኢትዮጵያንና የጃፓንን ግንኙነት በሙዚቃ ለማጠናከር በተደረገ ውድድር ተመርጣ ወደ ጃፓን ተጉዛለች። በቆይታዋም ቶኪዮ በሚገኝ የሙዚቃ ት/ቤት የድምጽ ስልጠና በመውሰድ በጃፓንኛ ያቀነቀነች ሲሆን ከዝነኛ የጃፓን ድምጻዊ ጋር በመሆን ዝግጅቷን በተለያዩ ከተሞች ተዘርዋውራ ስታቀርብ ከመቆየቷም በተጨማሪ በጃፓንኛ ነጠላ ዜማ ሰርታለች። ቲቪ አሳሂ በተባለ የቴሌቭዥን ጣቢያም ለአራት ወራት ያህል የተላለፈ አጠቃላይ ጉዞዋን የተመለከተ ሳምንታዊ ፕሮግራም ሰርታለች። “ይህ አጋጣሚ መክሊቴን ፍለጋ ከቆፈርኩባቸው ቦታዎች አንዱና የልጅነት ጀብዱዬ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ሌላ ታላቅ አጋጣሚ ፈጥሮልኝ አልፏል” ትላለች።

ሜሮን ግጥሞቿን በበርካታ መድረኮች፣ መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከማቅረብ ባሻገር በ1999 ዓ.ም “ዙረት” የተሰኘ የግጥም መድበል አሳትማ ለንባብ አብቅታለች። በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ውክልናም የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወጣት ጀግኖች ተሸላሚ በመሆን በወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ከነበሩት ከክቡር ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እጅ የሜዳሊያ ሽልማት ተቀብላለች።
ሜሮን ከሁለት እስከ አምስት አመታት ያህል በመድረክ ላይ በቆዩ የሙሉ ሰአት ቴአትሮች ላይ በመሪ ተዋናይነት ሰርታለች። እነዚህም
ፍሬሽማን፣ ትሩፋልዲኖ፣ መስተፋቅር፣ ሰማያዊ ዓይን በሃገር ፍቅር ቴአትር፤ እልባት በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ፤
ቅጥልጥል ኮከቦች በብሄራዊ ቴአትር ናቸው። በአንድ ቀን ሁለት የተለያዩ ቴአትሮችን በሁለት ተለያዩ መድረኮች ላይ ለአመታት የተጫወተች ሲሆን በ2ኛው የተስፋ ኢንተርፕራይዝ ሃገር አቀፍ የቴአትር ፌስቲቫል የሴት ኮከብ ተዋናይት ዘርፍ ተሸላሚ ሆናለች። በአሜሪካም በሚኔሶታ ግዛት የፍሪንጅ ቴአትር ፌስቲቫል ላይ ተሳትፋ ኢትዮጲያዊት ገጸ ባህሪ ወክላ በመጫወት የሀገሯን ባህል አስተዋውቃለች።

“የቴሌቭዥን ድራማዎች ከተመልካች ጋር የበለጠ እንድተዋወቅ አድርገውኛል” የምትለው ሜሮን ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም በተከታታይነት በኢትዮጲያ ቴሌቭዥን ሲተላለፉ በቆዩ ገመና አንድ፣ ገመና ሁለትና ዳና በተሰኙ ሳምንታዊ ድራማዎች ላይ ተወዳጅ ገጸ ባህሪያትን ወክላ በመጫወት ትታወቃለች።
አንድ ዕድል፣ ፊደል አዳኝ፣ ኤልዛቤል፣ የእግር ዕጣ፣ ዱካ፣ ይሉኝታ፣ቤተልሄም፣ ሄሎ ኢትዮጵያ፣ ዲፕሎማት፣ ጊዜ ግዙን፣ የተከፈለበት፣ ትራፊኳ እና ድፍረት የተወነችባቸው ፊልሞች ሲሆኑ የተከፈለበት በድርሰት፣ በዝግጅትና በፕሮዲውሰርነት ተሳትፋለች። በዚህም በኢትዮጲያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል የተመልካች ምርጫ ፊልም አሸናፊ እንዲሁም በቤተልሄም ምርጥ ረዳት ሴት ተዋናይት ዘርፍ ተሸላሚ ሆናለች። ከሃገር ወጪም በጀርመን የበርሊን ፊልም ፌስቲቫልና በአሜሪካ የሰንዳንስ ፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ተገኝታ በድፍረት ፊልም “የ2014 መታየት ያለባቸው የተመረጡ ተዋንያን” ዝርዝር ውስጥ ተካታለች።

በሬዲዮ ድራማ የዘመን ችግኞች እና ቀጭን ፍቅር በተሰኙ ተከታታይ ድራማዎች ላይ በትወና፤ ቃና ዜማ የተሰኘ ሳምንታዊ የመዝናኛ ፕሮግራም (ራዲዮ ፋና) በአዘጋጅና አቅራቢነት ለ2 ዓመታት ሠርታለች።

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.