Logo
FIDEL POST NEWS
ታላቁ የጨረቃ ግርዶሽ በኢትዮጵያ ሰማይ !

ዛሬ ጳጉሜን 2 ምሽት ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ምስራቅ አፍሪቃ፣ ምስራቅ አውሮጳ ፣ ማዕከላዊ እስያ ፣ ምዕራባዊ ኦሽኒያ እና በከፊል ሩቅ ምስራቅ እስያ አስደናቂ የሆነ ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ ይታያል።

ይህ ክስተት ጨረቃ በመሬት ሙሉ ጥላ ውስጥ ስታልፍ ደማቅ ቀይ ቀለም ስለምትይዝ " ቀይ ጨረቃ " (Blood Moon) በመባል ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ውስጥ እንደምንገኝበት አካባቢ የግርዶሹ አተያይ ላይ መጠነኛ ልዩነት ይኖራል። እስቲ ይህ ግርዶሽ እንዴት እንደሚከሰት እና በሀገራችን ክፍሎች ያለው ልዩነት ምን እንደሆነ በትክክለኛው መረጃ ላይ ተመስርተን እንመልከት።

የጨረቃ ግርዶሽ እንዴት ይከሰታል ?

የጨረቃ ግርዶሽ የሚከሰተው ፀሀይ፣ መሬት እና ጨረቃ በአንድ መስመር ላይ ሲሰለፉና መሬት በፀሀይ እና በጨረቃ መካከል ገብታ ጥላዋን ጨረቃ ላይ ስታሳርፍ ነው።

የመሬት ጥላ ሁለት አይነት ነው ፦
° የመሬት ድብዝዝ ጥላ (Penumbra) የውጪውና ደብዛዛው ሲሆን፣
° የመሬት ጽልም ጥላ (Umbra) ደግሞ ዋናውና ጥቁሩ ጥላ ነው።

ሙሉ ግርዶሽ የሚባለው ጨረቃ ሙሉ በሙሉ በጽልም ጥላ ውስጥ ስትገባ ነው።

በኢትዮጵያ የግርዶሹ አተያይ ልዩነት ፦

1. ምስራቃዊ እና መካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍል (ግርዶሹን ሙሉ በሙሉ የሚያዩ)

እነዚህ አካባቢዎች (#አዲስ_አበባን ጨምሮ) ግርዶሹ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ ያሉትን ሁሉንም ሂደቶች ያያሉ። ግርዶሹ ሲጀምር ጨረቃ ቀድማ ሰማይ ላይ ወጥታ ስለምትገኝ፣ የመጀመሪያው የብርሃን መደብዘዝ (በድብዝዝ ጥላ)፣ ወደ ጽልም ጥላ መግባቷ፣ ሙሉ በሙሉ ቀይ መሆኗ እና ከጥላ መውጣቷን በሙሉ መመልከት ይችላሉ።

በዚህ ምድብ ስር የሚገኙ ከተሞች ፦
- አዲስ አበባ፣
- ደብረ ብርሃን፣
- ደሴ፣ መቐለ፣
- አዲግራት፣
- አክሱም፣
- ሰመራ፣
- ድሬዳዋ፣
- ሐረር፣
- ጅግጅጋ፣
- አዳማ፣
- አሰላ፣
- ሻሸመኔ፣
- ሀዋሳ፣
- አርባ ምንጭ፣
- ወልቂጤ፣
- ሮቤ፣
- ጎዴ፣ ሞያሌ እና ሌሎችም።

2. ምዕራባዊ የኢትዮጵያ ክፍል (የግርዶሹ የመጀመሪያ ክፍል የማይታይባቸው ቦታዎች)

እንደ ጋምቤላ፣ ባህር ዳር ፣ ሚዛን ተፈሪ እና አሶሳ ያሉ የምዕራብ ኢትዮጵያ ከተሞች የግርዶሹ ዋና ዋና ክፍሎች የሆኑትን ከፊል ግርዶሹን እና ሙሉ ግርዶሹን በሙሉ ያያሉ።

ልዩነቱ የሚመጣው በመጀመሪያው የድብዝዝ ግርዶሽ (Penumbral Eclipse) ወቅት ነው፦
የድብዝዝ ግርዶሹ የሚጀምረው ምሽት 12:28 ሰዓት (6:28 PM) ላይ ነው።

በዚህ ሰዓት እንደ ጋምቤላ ባሉ ምዕራባዊ ከተሞች ጨረቃ ከአድማስ በታች ስለምትሆን አትታይም።

በጋምቤላ ጨረቃ ከአድማስ በላይ ወጥታ መታየት የምትጀምረው ምሽት 12:39 (6:39 PM) ላይ ነው። ይህ ማለት የጋምቤላ እና ሌሎች የምዕራብ ኢትዮጵያ ተመልካቾች ጨረቃን ማየት ሲጀምሩ፣ እሷ ለ11 ደቂቃ ያህል በድብዝዝ ጥላ ውስጥ ተጉዛለች ማለት ነው። ስለዚህ፣ የሚያመልጣቸው የግርዶሹ የመጀመሪያ 11 ደቂቃ ብቻ ሲሆን፣ ይህ ክፍል ደግሞ በዓይን በቀላሉ የማይለይ የብርሃን መቀነስ ብቻ ነው።

ዋናው ነጥብ በጣም አስደናቂዎቹ የግርዶሹ ክፍሎች (ከፊል እና ሙሉ ግርዶሽ) ከመጀመራቸው በፊት ጨረቃ በሰማይ ላይ በደንብ ከፍ ስለምትል፣ ከነዚህ አስደናቂ ሂደቶች አንድም አያመልጣቸውም።

በዚህ ምድብ ስር የሚገኙ ከተሞች፦
- ጋምቤላ፣
- ጎንደር፣
- ባህር ዳር፣
- አሶሳ፣
- መተማ፣
- ደምቢ ዶሎ፣
- ነቀምት፣
- ጅማ፣
- ሚዛን ተፈሪ፣
- ቦንጋ፣
- ጂንካ እና ሌሎችም።

የግርዶሹ የጊዜ ሰሌዳ (በአዲስ አበባ ሰዓት አቆጣጠር) የድብዝዝ ግርዶሽ መጀመሪያ ፦ ምሽት 12:28  (6:28 PM)
ከፊል ግርዶሽ መጀመሪያ (ወደ ጽልም ጥላ ስትገባ) ፦ ምሽት 1:27  (7:27 PM)
ሙሉ ግርዶሽ መጀመሪያ (ቀይ መሆን ስትጀምር)፦ ምሽት 2:30  (8:30 PM)
የግርዶሹ ማክሲመም (ጥልቅ ቀይ ስትሆን) ፦ ማታ 3:11  (9:11 PM)
ሙሉ ግርዶሽ ማብቂያ፦ ማታ 3:52  (9:52 PM)
ከፊል ግርዶሽ ማብቂያ፦ ማታ 4:56  (10:56 PM)
የድብዝዝ ግርዶሽ ማብቂያ፦ ማታ 5:55  (11:55 PM)

ማሳሰቢያ ፦ ይህንን አስደናቂ የሰማይ ክስተት ለመመልከት ምንም አይነት ልዩ መነጽር አያስፈልግም። ነገር ግን ከሥነ ፈለካዊ ትንበያው በተጨማሪ ያሉበት አካባቢ እንደሚኖረው የደመና ሽፋን ይሄንን ክስተት የማየት ዕድሉ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል።

ግርዶሹን በኢ.ስ.ሳ.ሶ የዩቲዩብ ገጽበቀጥታ መመልከት ይቻላል።

Credit - Ethiopian Space Science SocietyEthiopian Space Science SocietyA nonprofit, civil society organization that promotes and advances astronomy, space science, and space technologies in Ethiopia through space awareness activities, educational programs, and a nationwide developmental program.
9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.