Logo
SeledaPost
የደመወዝ ጭማሪን ተከትሎ የሚከሰቱ የዋጋ ንረትን ለመግታት ማስጠንቀቂያ ተሰጠ::

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ሚኒስቴሩ፣ በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው የደመወዝ ጭማሪ፣ የሠራተኞችን ኑሮ ለማሻሻል ያለመ አዎንታዊ እርምጃ መሆኑን ገልጿል። ይሁን እንጂ፣ አንዳንድ ነጋዴዎች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የዋጋ ንረት ለመፍጠር እና ሰው ሠራሽ የምርት እጥረት ለማስከተል ሲሞክሩ መታየቱን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ እንዳለው፣ "በገንዘብ ፍቅር የታወሩ" ጥቂት ነጋዴዎች፣ የሠራተኞችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የተደረገውን ጥረት በመጠቀም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት መሯሯጣቸው ተስተውሏል።
ይህንን ድርጊትም "አሳፋሪ" ሲል አውግዟል።

በመሆኑም፣ ሚኒስቴሩ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ፣ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ፣ ምርት የሚደብቁ ወይም አላግባብ የሚያከማቹ ነጋዴዎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

በተጨማሪም፣ የንግድ መዋቅሩ ከፀጥታ እና ከፍትህ አካላት ጋር በመተባበር የገበያ ማረጋጋት ሥራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል እና በአጥፊዎች ላይም አስተማሪ እርምጃ እንዲወስድ መመሪያ አስተላልፏል።

Via የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር

Seledadotio
Seledadotio
12 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.