Logo
Getu Temesgen
የኪነ ጥበቡ ዋርካ አርፈዋል
#ethiopia | አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።

በሕክምና በተለያዩ ሆስፒታሎች ይከታተሉ ነበር።

***

ጋሽ ደቤ !

ተዋናይ ፣ኮሜዲያን፣ አዘጋጅ ሆኖ ለረዥም ዓመታት አገልግሏል፡፡ በመድረክ ፣ በሬዲዩ፣ በቴሌቪዥን፣ በፊልም ስራ እና በጋዜጠኝነት ሙያ ሠርቷል ። በአፍሪካ የመድረክ ሙያተኞች ማህበር በሊቀመንበርነት መርቷል ፣ በአትላንታ ጆርጂያ በበረከተው የሙያው ሥራ ኖቬምበር 24 ቀን በስሙ ተሰይሞለታል። (ጋሽ ደቤ) በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በህይወት ካሉት አርቲስቶች ግንባር ቀደሙና አንጋፋው ነው።

መጀመሪያ በቴያትር የታዩት በመንግስቱ ለማ በተጻፈው ያላቻ ጋብቻ ሲሆን ከዚያ በአንዳንድ እንግሊዝኛ ትርኢት (The game of chess, ‘Waiting for Godot’) እንዲሁም በራዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን ተጫወቱ።

አርቲስት ደበበ እሸቱ (ጋሽ ደቤ) ለታሪክ የሚተላለፉ ህያው ስራዎች ሰርቷል እስቲ ጋሽ ደቤ ከሰራቸው ስራዎች ውስጥ በጥቂቱ እንያቸው፤ በሃገር ውስጥ ካለው ታዋቂነትና ለሙያው ካደረገው አስተዋጽኦ ለመጠቀስ ያህል ፡-

በቤተኪነጥበባት ወቴአትር፡-

ያላቻ ጋብቻ ተዋናይ
ሮሚዎባ ዡልየት ተዋናይ
ጠልፎ በኪሴ ተዋናይም አዘጋጂም
ዳንዴው ጨቡዴ ››
ዘ ጌም ኦፍ ቼዝ (በእንግሊዝኛ) ተዋናይ
ኦቴሎ (በአንግሊዝኛ) ተዋናይም አዘጋጂም
አዳ ኦክ አራክል (በእንግሊዝኛ)ከሎ.ጸ.ገ.መ ተዋናይ
በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ(ብሔራዊ) ቴአትር፡-
የበጋ ሌሊት ራዕይ ተዋናይ
አንድ ዓመት ከአንድ ቀን ተዋናይ
እናት ዓለም ጠኑ ተዋናይ
ኪንግ ሊር ተዋናይ
ዋናው ተቆጣጣሪ ተዋናይ
ጠያቂ ተዋናይ አዘጋጅ
በቀይካባ ስውር ደባ አዘጋጅ
ተሓድሶ አዘጋጅ
የአዘውንቶች ክበብ አዘጋጅ ተዋናይ
በሃገር ፍቅር ቴአትር፡-
ጠልፎ በኪሴ አዘጋጅ/ተዋናይ
የወፍ ጎጆ ተዋናይ
ኪንግ ሊር ተዋናይ
የቬኒሱ ነጋዴ ተዋናይ
ናትናኤል ጠቢቡ ተዋናይ
ድብልቅልቅ ተርጓሚ/ ተዋናይ
ማዕበል ተርጓሚ አዘጋጅ
በፊልም በሃገርና በዓለም አቀፍ፡-
ዘ ሴይለር ፍሮም ጂብራልታር
ሻፍት ኢን አፍሪካ
ጉማ
ዚ አፍሪካን ስፓይ
ዜልዳ
አፍሪካ
ዘግሬቭ ዲገር
ዘ ግሬት ሪቤሊየን

እነዚህ ለምሳሌ ያህል የቀረቡ እንጂ የደበበ ስራዎች በርካቶች ናቸው፡፡ ከመድረክና ፊልም ስራዎቹ ባሻገር ተማሪዎችም አሰልጥኗል፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተዋንያን ስልጠና ማዕከል ሲያቋቁሙ ከመምህራኖቹ መሃልና በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው መምህር ደበበ ሲሆን ለተማሪዎቹም መማርያ እንዲሆን የተረጎመው የስታንስላቭስኪ የተዋናይ ሀሁ ለበርካታዎች የሙያ ተማሪዎች የሙያቸው ፊደል መቁጠርያ ሆኖ ይገኛል፡፡

በትርጉም በኩልም ደበበ ከቴአትር፡-

ያልታመመው በሽተኛ
ድብልቅልቅ
ጎርፉ
ከመጽሐፍ ደሞ
የዳዊት ወልደጊዮርጊስን
የደም እንባ
የራሱን ወጥ ሥራ በተመለከተ
የእምነቴ ፈተና
ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው

ደበበ ለአፍሪካ ጥበብ ያለውን አመለካከትና ግንዛቤ ከቅኝ ገዢዎች ትርጓሜ ለማውጣትና ሦስተኛው ዓለም ኋላ ቀር ሲባልም በኤኮኖሚና በቴክኒዮሎጂ እንደሆነ፤ ይህም የሆነው ነጩ የአፍሪካን የዋህነት፤ እንግዳ ተቀባይነትና ሩህሩህነት መንጠላጠያ በማድረግ ቅኝ አድርገው ህሊናውን ስለዘጉበትና ስላሰሩት መሆኑን፤ በባህል በኩል ግን ጨርሶ ሊደርሱበት የማይችሉትና ሊያጠፉትም ያደረጉት ሙከራ ዋጋ ቢስ ሆኖ እንደቀረ የሚያስረዳ ጥናታዊ ጽሁፍ በማቅረብ ተቀባይነትን አግኝቶ ድል ያደረገና፤ ቀደም ሲል የጀመረውን ትግል አጠናክሮ በመቀጠል በ1985 ዓ.ም እንደ አውሮፓውያን ቆጣጠር በርሊን ላይ በተካሄደው የዩኔስኮ የባህል(አይ ቲ አይ) ኢንተርናሽናል ቴአትር ኢትዮጵያን ወክሎ በመገኘት በአፍሪካ ውስጥ የመጀመርያው ፕሮፌሽናል ቴአትር ቤት የሃገር ፍቅር ቴአትር መሆኑን በማስረጃ አስደግፎ ተቀባይነትን አገኝቷል፡፡

በዚሁ ዓመት የዩኔስኮ የባሕል ክፍል አይ ቲ አይ የአፍሪካ ተጠሪ ሆኖ በመመረጥ፤ በዚያው ዘመን ዝምባብዌ ላይ በሚካሄደው ቴአትር ለልማትና ዕድገት ወርክሾፕ ላይ በመሪነት እንዲገኝ በዩኔስኮ ተወክሎ በመሄድ ወርክሾፑን በአጥጋቢ ችሎታውና የአመራር ብቃቱ ከመፈጸሙም ባሻገር ለብዙ ጊዜ ተሞክሮ ሲወድቅ ሲነሳ የነበረውን የአፍሪካ የመድረክ ባለሙያዎች ማሕበርን አስተባብሮ በማቋቋም የማሕበሩም መስራች ፕሬዜዳንት ሆኖ ለ12 ዓመታት መርቷል፡፡ አሁንም መሥራች ፕሬዚዳንት በመባል ይጠራል፡:

ደበበ በችሎታውና በብቃቱ በማስተባበር ችሎታው ዩኔስኮ ዓለም አቀፍ የቴአትር ኢንሳይክሎፒዲያን ለማዘጋጀት ሲወስን ደበበንም አፍሪካን በመወከል የኤዲቶርያል ቦርድ አባል አድርጎ መድቦት ሥራውን በሚገባ ተወጥቷል፡፡

ደበበ ቴአትር ለልማትና ለእድገት በሚል የሚታወቀውን የቴአትር ዲሲፕሊን ስልጠና ለበርካታ ሃገራት ባለሙያዎች ያስተማረ ሲሆን በርካታ ወርክሾፖችም በየሃገራቱ እየተጋበዘ መርቷል፡፡ ይህን ዘዴ ካዋቀሩትም አምስት አፍሪካዊ ባለሙያዎች አንዱ ደበበ ነው፡፡

ወርክሾፕ የሰጠባቸው ቦታዎች፤ ታንዛኒያ፤ ኡጋንዳ፤ ኬንያ፤ማላዊ፤ ኮንጎ ብራዛቪል፤ አይቮሪ ኮስት፤ ካሜሩን፤ ናይጄርያ፤ አይርላንድ፤ ብራዚል፤ ሰሜን አሜሪካ፤ እንግሊዝ፤ ኩባ፤ በርሊን፤ ካናዳ ይገኙበታል፡፡

ደበበ ላለፉት ከ40 በላይ ዓመታት በቴአትር ጥበብ ውስጥ ኖሮ በ1995 በተካሄደው ሃገራዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ‹‹ቀስተደመና›› የፖለቲካ ፓርቲን ተቀላቅሎ፤ በኋላም ቅንጅት ሲፈጠር የምክር ቤት አባልና የሕዝብ ግንኙነት በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ቅንጅትን ለድል ያበቃ፤ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ዝግጅቶቹ ቅንጅትን ያገዘፉ ነበሩ፡፡በዚህም ከሌሎች አመራሮች ጋር ለአንድ ዓመት ከአስር ወራት ለእስር ተዳርጓል፡፡ እንዲሁም በ2002 በድጋሚ ለአንድ አመት ታስሮ ተፈቷል፡፡

ደበበ በሃገሩ ለመሸለም ባይበቃም በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን ለሽልማቶች የበቃ ባለሙያ ነው፡፡ ለዚሁ የሙያ አስተዋጽኦ ክፍተኛው ክብሩ በአትላንታ ጆርጂያ ኖቬምበር 24 የደበበ እሸቱ ቀን ተብሎ እንዲሰየም የከተማው ምክር ቤት ማጽደቁ ነው፡፡

ጋሽ ደቤ ጋደኛም፤ ሚስትም ከሆነችው ከአልማዝ ደጀኔ ጋር 4 ልጆች እና 6 የልጅ ልጆች አሉት።

ነፍስ ይማር

10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.