Logo
ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal
በነቀምቴ ከተማ በማተሚያ ቤት ውስጥ ሐሰተኛ ገንዘብ ሲያትም የነበረው ግለሰብ እጅ ከፍንጅ ተያዘ

በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር አንድ የህትመት ቤት ባለቤት የሆነው ወጣት የሁለት መቶ ብር የሐሰተኛ ገንዘብ ሲያትም ከሕዝብ በደረሰ ጥቆማ መሰረት እጅ ከፍንጅ መያዙን የከተማው አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና መምሪያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ሀላፊ ኮማንደር ፍሮምሳ ቂጤሳ እንደገለጹት ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 11:30 ገደማ በጨለለቂ ቀበሌ በሚገኘውና ፍራኦል አብዲሳ ገለታ በተባለው ወጣት በሚመራው የህትመት ቤት ውስጥ የሐሰት ገንዘብ እየተዘጋጀ መሆኑን ከሕዝብ ጥቆማ ይደርሳቸዋል።

በጥቆማው መሠረት ስፍራው ድረስ በመሄድ በተደረገው ፍተሻ የተሰጠው ጥቆማ ትክክል ሆኖ መገኘቱንና የሁለት መቶ ብር የሐሰት ገንዘብ በፎቶ ኮፒ ማሽን እየተባዛ በመውጣት ላይ እያለ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የተባዛው የሐሰት ገንዘብ መጠን 33 ሺህ 600 ብር መሆኑንና ተጠርጣሪውም በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጸዋል።እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች የሕብረተሰቡን ኢኮኖሚ ከመጉዳታቸው ባሻገር የአገርንም ኢኮኖሚ የሚጎዱ በመሆናቸው ሕብረተሰቡ መሰል ወንጀሎችን በሚመለከትበት ጊዜ ለጸጥታ አካላት ጥቆማ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።

ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘም ፖሊስ ከዐቃቤ ሕግ ጋር በመተባበር ምርመራ መጀመሩንና ተጣርቶ የሕግ የበላይነት እንደሚረጋገጥ ምክትል ኮማንደር ፍሮምሳ ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡ በግዢና ሽያጭ ወቅት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል ሲል የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

#ዳጉ_ጆርናል
11 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.