Logo
SeledaPost
በሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር ወንጀል በተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ላይ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ክስ መመስረቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ2016/2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን ከተለያዩ የዘርፉ ተጠሪዎች ጋር እየገመገመ ባለበት መድረክ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ተወካይ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በሞባይል ባንኪንግ አማካኝነት ከ116 ግለሰቦች ላይ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በሞባይል ባንኪግ በማጭበርበር ወንጀል በተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ላይ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደተመሰረተባቸው ገልጸዋል።

ተከሳሾቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከሌሎች የግል ባንኮች የሚደውሉ በማስመሰል እንዲሁም የኮምፒውተር ሥርዓትን በመጠቀም አሳሳች መረጃዎችን በማሰራጨት ወንጀሉን እንደፈጸሙ ፖሊስ መግለጹን አንስተዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት የቀረበው ክስ እንደሚያብራራው፤ ተጠርጣሪዎቹ ማንነታቸውን በመሰወርና ሀሰተኛ ሰነዶችን እና መታወቂያዎችን በማዘጋጀት እና በመጠቀም የተበዳዮችን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረበው ክስ በዋናነት በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ እና የኮምፒዩተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 958/2008ን እንዲሁም የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003ን የተላለፉ መሆናቸውን ይገልጻል።

ለወንጀል ድርጊቱ ማስፈጸሚያነት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ በርካታ የባንክ አካውንቶች፣ የሞባይል ቀፎዎች፣ ሲም ካርዶች እና ኮምፒውተሮች እንደተያዙ መገለጹን የኢቢሲ ዘገባ አመላቷል፡፡

ጉዳዩን ለማጣራትም ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

Seledadotio
Seledadotio
1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.