Logo
FastMereja
1 ሚሊዮን ብር የሚያስገኘው የባህል አምባሳደር አዋርድ 2019 የፍጻሜ ውድድር ሊካሄድ ነው
#fastmereja I ​በባህላዊ ትወና፣ በሀገርኛ ሙዚቃና በውዝዋዜ ዘርፎች የተዘጋጀው እና የ1 ሚሊዮን ብር ሽልማት የሚያስገኘው «የባህል አምባሳደር አዋርድ 2019» የመጨረሻ መርሃ ግብር ህዳር 5 ቀን 2019 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በደመቀ ሁኔታ እንደሚካሄድ ተገለጸ። በዮድ አቢሲኒያ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ መረዳት እንደተቻለው፤ ውድድሩ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር «ክብር ያለው እኛ ጋር ነው» በሚል መሪ ቃል በ77 ተወዳዳሪዎች ተጀምሮ፣ አሁን ላይ በሦስት የውድድር ምድቦች ተለይተው የመጨረሻውን ዙር የተቀላቀሉ 15 ምርጥ ተወዳዳሪዎችን አሳልፏል።

​በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አዘጋጆቹ እንደገለጹት፤ የፍጻሜው አሸናፊዎች የሚለዩት በ60 በመቶ የባለሙያ ዳኞች ግምገማ እና በ40 በመቶ የህዝብ ድምፅ ተደምሮ ይሆናል። በዚህም መሰረት ለውድድሩ አንደኛ ለወጣ ተወዳዳሪ የ1 ሚሊዮን ብር፣ ለሁለተኛ 300 ሺህ ብር እንዲሁም ለሦስተኛ ደረጃ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከት ተነግሯል፡፡ ከዚህ ባለፈም ሦስቱም አሸናፊዎች ወደ ሕንድ በመጓዝ የባህል ልምድ ልውውጥ የማድረግ ወርቃማ ዕድል እንደሚያገኙ የውድድሩ አዘጋጅ አቶ ዳንኤል ጥሩነህ አስታውቀዋል።

​በሌላ በኩል ተወዳዳሪዎቹ ያዘጋጁትን «ይህቺ ናት ሀገሬ» የተሰኘ ህብረ ዜማ በማህበራዊ ሚዲያ በተለየ የፈጠራ መንገድ የሚያስተዋውቅ ማንኛውም ማህበረሰብ አባል ከተወዳዳሪዎቹ ጋር ወደ ሕንድ የማቅናት ልዩ ዕድል እንደተመቻቸለት ይፋ ተደርጓል።

​በዝግጅት አደረጃጀትና አፈጻጸም ላይ ከአዘጋጆቹ ጋር በጋራ የሚሰራው የአጋፔ ኤቨንት ኦርጋናይዘርስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሚኪያስ ግርማ እንደተናገሩት፤ የመጨረሻውን ፕሮግራም ታሪካዊው ሮሃ ባንድ ከተወዳዳሪዎች እንዲሁም ከአንጋፋ እና ታዋቂ ድምፃውያን ጋር በመሆን በሙዚቃ ያደምቀዋል። ይህ ውድድር የወጣቶችን ችሎታ ከማበረታታት ባሻገር የኢትዮጵያን ባህላዊ እሴቶች ለማስተዋወቅ፣ የባህል ልምድ ልውውጥን ለማጠናከር እና ለወጣት ተሰጥኦዎች አዲስ የዕድል በር ለመክፈት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ከወጣው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።

10 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.