Logo
ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal
በሜክሲኮ በአውሎ ነፋስና ከባድ ጎርፍ የነዋሪዎች ህይወት አለፈ

በሜክሲኮ የፓሲፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ በአውሎ ነፋስ ሲሞንና በሞቃታማ አውሎ ነፋስ ሬቸል ምክንያት በደረሰው ከባድ ዝናብና ጎርፍ ቢያንስ አምስት ሰዎች ሲሞቱ፣ ሌሎች ደግሞ መጥፋታቸው ተዘግቧል። አደጋው ቤቶችንና መንገዶችን ከመጉዳቱም በላይ፣ ነዋሪዎችን ከተጥለቀለቁ አካባቢዎች ለማውጣት በሄሊኮፕተር የማዳን ሥራ እንዲካሄድ አስገድዷል።

ከሞቱት መካከል አንድ የ71 ዓመት አዛውንት በጉሬሮ ግዛት በሚገኘው ቺልፓንሲንጎ ከተማ በከባድ ዝናብ ምክንያት የፈረሰ ግድግዳ ወድቆባቸው ሕይወታቸው አልፏል። በባጃ ካሊፎርኒያ ግዛት ደግሞ በሬቸል ያስከተለው ጎርፍ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላትን፣ ሁለት ሕፃናትን ጨምሮ፣ ሕይወት እንዳሳጣ ባለሥልጣናት ገልጸዋል። በተመሳሳይም በኤንሴናዳ አካባቢ በጎርፍ የተጠቁ 32 ሰዎች በሄሊኮፕተር ከአደጋው ቦታ መውጣታቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል፣ አውሎ ነፋስ ሲሞን የባህር ዳርቻውን እያጠቃ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚገኙ ቤቶችና መንገዶች በውኃ ተጥለቅልቀዋል፤ የኤሌክትሪክ መስመሮችና ዛፎችም ወድቀዋል። ሲሞን ወደ ሜክሲኮ ምዕራባዊ ዳርቻ እየተጠጋ ቢሆንም፣ ኃይሉ ከአራተኛ ደረጃ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ማለቱ ተዘግቧል። ይሁን እንጂ ከባድ ዝናብ፣ የመሬት መንሸራተትና አደገኛ የባህር ሞገድ ስጋት እንዳልተወገደ የአየር ሁኔታ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

ባለሥልጣናት በአደጋው ሊጠቁ በሚችሉ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ከጎርፍ አደጋ እንዲጠነቀቁ ጥሪ አቅርበዋል። በተለይም በወንዞችና በጅረቶች አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች አስፈላጊ ሲሆን ከአደጋ ቦታዎች እንዲወጡ ተመክረዋል። በሜክሲኮ የተከሰቱት እነዚህ አውሎ ነፋሶች በዚህ ዓመት በፓሲፊክ ውቅያኖስ የተመዘገበው ከፍተኛ የአውሎ ነፋስ እንቅስቃሴ አካል ሲሆኑ፣ የኤል ኒኞ የውቅያኖስ ሙቀት መጨመር ክስተትም ለአየር ሁኔታው መጠናከር አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ ባለሙያዎች ያመለክታሉ መባሉን ዘ ጋርዲያን አስነብቧል፡፡

በቤዛዊት አራጌ
#ዳጉ_ጆርናል Photo
2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.