Logo
YenetaTube
የራያ ህልውና አደጋና የአብን አስቸኳይ የትኩረት ጥሪ

አብን በራያ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን መዋቅራዊ ጭቆና፣ የማንነት ክህደት እና የተደራጀ ማፈናቀል አስመልክቶ ዛሬ ጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም. መግለጫ አውጥቷል።

ንቅናቄው በራያ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው መሠረታዊ የህልውና ስጋትና የጸጥታ መደፍረስ ወደ አደገኛ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን ገልጿል።

በመግለጫው እንደተመለከተው፣ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ከአካባቢው መውጣትን ተከትሎ ሕወሓት ሰፊ በቀል መፈጸሙ እና ከመቶ ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል።

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላም እንኳ በአካባቢው ዳግም በተቀሰቀሰው ግጭት የንጹሐን ሕይወት ማለፉ እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱ ተገልጿል።

አብን በመግለጫው እንደገለፀው ራሱን "የትግራይ ሰላም ሠራዊት (TPF)" ብሎ የሚጠራው የታጠቀ ቡድን ወደ ቀያቸው በመመለስ ላይ በነበሩ ተፈናቃዮችና እነሱን ለመቀበል በተሰባሰቡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ካህናት እና ወጣቶች ላይ ተኩስ በመክፈት ጉዳት አድርሷል ሲል ወንላል

ቡድኑ በራያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ላይ ድንገተኛ ተኩስ የከፈተ ሲሆን፤ መስከረም 23 ቀን 2019 ዓ.ም. ሕፃናትና እናቶች የተሳፈሩባቸውን ከ20 በላይ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በማገት ለከባድ መሣሪያ ጥቃት ሰለባ አድርጓል።

አካባቢውን በኃይል በመቆጣጠር ትምህርት ቤቶች በአማርኛ ቋንቋ እንዳያስተምሩ ማገዱን እና ሕዝቡን የማስፈራራት ስራ እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

አብን የራያ ሕዝብ ጥያቄዎች ዘላቂ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ አካባቢውን ከየትኛውም የታጠቀ ኃይል ነፃ በማድረግ፣ ሕዝቡ የራሱን ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያቋቁም፤ "የትግራይ ሰላም ሠራዊት" የሚባለው ቡድን ያለ ቅድመ ሁኔታ ከአካባቢው እንዲወጣና ተፈናቃዮች ያለምንም ስጋት ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ አሳስቧል።

የአማራ ክልል መንግሥት ክልሉ በሕዝቡ ላይ እየተፈጸመ ያለውን መዋቅራዊ በደል በዝምታ መመልከቱን አቁሞ ለሕዝቡ ሰብአዊ ደኅንነትና መብት የማያወላውል አቋም እንዲይዝ ጥሪ ቀርቧል።

አብን የራያ ሕዝብ የሕዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ከፋፋይ ሴራዎች ራሱን እንዲጠብቅ እና ማህበረሰባዊ አደረጃጀቶቹን አጠናክሮ ከፌዴራል ጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አካባቢውን እንዲጠብቅ ጠይቋል።

ድርጅቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር (OHCHR) በአካባቢው የተፈጸሙትን ጥቃቶች እና ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ የተደረገበትን ክልከላ በአካል በመገኘት ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሂዱ ጥሪ ቀርቧል።

3 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.