Logo
Getu Temesgen
የቅዱስ ላሊበላን ታሪክና መንፈሳዊ ትርጉም የሚዳስስ መጽሐፍ በሁለት ቋንቋዎች ተዘጋጀ
‎
‎#ethiopia | የቅዱስ ላሊበላን ታሪክ፣ መንፈሳዊ ትርጉምና ከአንድ ወጥ አለት ቤተ ክርስቲያናቱን ልዩ ጥበብ ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ መጽሐፍ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተዘጋጅቷል።
‎
‎በቅዱስ ላሊበላ ተወልደው አድገው ከልጅነታቸው ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የቆዩት ቀሲስ ፈንታ ታደሰ ዘ ላሊበላ፣ የከተማዋን ታሪክና መንፈሳዊ ቅርሶች በማጥናት፣ በመጻፍና በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ለሕዝብ በማድረስ ለዓመታት ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸው በተለይም የቅዱስ ላሊበላን ታሪክና በአካባቢው የሚገኙ መንፈሳዊ ቦታዎችን ለሰፊው ሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ የጀመሩትን ጥረት በአሁኑ ወቅትም እያስቀጠሉ ይገኛሉ።
‎
‎ቀሲስ ፈንታ እንደገለጹት፣ ከዓመታት በፊት የቅዱስ ላሊበላን ታሪክ በቴፕ ካሴት በመቅዳት ለሕዝብ የማቅረብ ሥራ ጀምረዋል። በኋላም በቪዲዮና በቪሲዲ በመቅረጽ የታሪኩን ይዘት ከምስል ጋር በማቅረብ፣ ሰዎች ስለ ቅርሶቹ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ሠርተዋል። ይህ ጥረት በኋላ ወደ መጻሕፍት ጽሕፈት የተሸጋገረ ሲሆን፣ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በአማርኛ ቋንቋ የተለያዩ መጻሕፍትን በማዘጋጀት ስለ ቅዱስ ላሊበላና ስለ አካባቢው ታሪክ የሚገኙ መረጃዎችን ለማሰባሰብና ለማቅረብ ጥረት አድርገዋል።
‎
‎የቀደሙት የታሪክ አዋቂዎች ያካፈሏቸውን ትረካዎች፣ የአካባቢውን ታሪካዊ መረጃዎችና የተለያዩ መጻሕፍትን በማንበብ ያገኟቸውን ግንዛቤዎች በማጣመር የቅዱስ ላሊበላን ታሪክ ለሰዎች በቀላሉ ሊገባ በሚችል መልኩ ለማቅረብ እንደሠሩ አስረድተዋል።
‎
‎አሁን ይፋ ለማድረግ የተዘጋጁት መጻሕፍት ከቀደሙት ሥራዎቻቸው የሚለዩበት ዋነኛ ገጽታ የቅዱስ ላሊበላን ታሪክ በእንግሊዝኛም ማቅረባቸው ነው። በአማርኛ የቀረበው መጽሐፍ «ቅዱስ ላሊበላ፡ በእምነት የታነጸ ቅዱስ ዓለት» የሚል ርዕስ ሲኖረው፣ የእንግሊዝኛው ርዕስ “A Sacred Rock Built by Faith” ነው። የሥራው ዋነኛ ዓላማ በዓለት ውስጥ ተቀርጸው የተሠሩትን ቤተ ክርስቲያናት ከሥነ ሕንፃ ጥበባቸው ባሻገር ባላቸው መንፈሳዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም ለማስረዳት መሆኑን ገልጸዋል።
‎
‎በቀሲስ ፈንታ እይታ፣ የቅዱስ ላሊበላ ቤተ ክርስቲያናት የግንባታ ጥበብ ብቻ ሳይሆኑ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙ ታሪኮችና መንፈሳዊ ምሳሌዎች በምድር ላይ በሕንፃና በቦታ አቀማመጥ የተገለጹበት ድንቅ ውጤት ናቸው። መጽሐፉም ይህንን ግንኙነት በማብራራት፣ በቅርሶቹ ውስጥ የተካተቱ መንፈሳዊ ትርጉሞችን ለአንባቢያን ለማስገንዘብ ይሞክራል።
‎
‎በተለይም በቅዱስ ላሊበላ የሚገኙት አሥሩ የዓለት ቤተ ክርስቲያናት በሦስት ምድቦች እንደሚታዩ በመግለጽ፣ በአንዳንድ የቱሪዝም ትረካዎችና በታሪክ ገለጻዎች የሚሰሙ የቁጥር ልዩነቶችን ለማብራራት ጥረት አድርገዋል። በተለይ ደብረሲና እና ጎልጎታ የሚባሉት ቦታዎች በአንድ ምድብ ውስጥ እንደሚቆጠሩ በማስረዳት፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ የታሪክ ገለጻ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
‎
‎መጽሐፉ ከቤተ ክርስቲያናቱ ብቻ በላይ በቅዱስ ላሊበላና በዙሪያዋ የሚገኙ ተራሮችን፣ የውኃ ማፋሰሻዎችንና ሌሎች መንፈሳዊ ትርጉም ያላቸውን ቦታዎችም ይዳስሳል። እነዚህ ቦታዎች ከምድራዊትና ከሰማያዊት ኢየሩሳሌም፣ ከኖኅ መርከብና ከሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኮች ጋር በምሳሌነት የሚገናኙበትን መንገድ ያብራራል። ይህም ቅዱስ ላሊበላን ከታሪካዊ ቅርስነቷ ባሻገር በመንፈሳዊ ትርጉም የተሞላች ስፍራ እንደሆነች ለማሳየት ያለመ ነው።
‎
‎ቀሲስ ፈንታ በተጨማሪም የቅዱስ ላሊበላን ታሪክ ሲያስጎበኙ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች አንዱ የታሪክ መረጃዎችን በትክክል ሳይመረምሩ ማቅረብ መሆኑን ጠቅሰዋል። አንዳንድ ጊዜ በመጻሕፍት የተጻፈውና በቦታው ላይ የሚታየው ሁኔታ በተለያየ መልኩ ሊተረጎም እንደሚችል በመግለጽ፣ አስጎብኚዎችና የታሪክ ጸሐፊዎች ምንጮችን በጥንቃቄ በማንበብና በማነጻጸር ለሕዝብ ትክክለኛ ገለጻ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።
‎
‎የመጽሐፉ ዝግጅት በአካባቢው ያሉ ታሪካዊ ትረካዎችን በመሰብሰብ፣ የተለያዩ የጽሑፍ ምንጮችን በማንበብና የቅርሶቹን አቀማመጥ ከመንፈሳዊ ትርጉማቸው ጋር በማገናኘት የተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል። በዚህም የላሊበላን ታሪክ ለማወቅ ለሚፈልጉ ተመራማሪዎች፣ ተማሪዎች፣ አስጎብኚዎችና ለሰፊው ሕዝብ ጠቃሚ የመረጃ ምንጭ እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል።
‎
‎መጽሐፉ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋዎች በአማዞን የሕትመት መድረክ ለአንባቢያን እንዲደርስ መዘጋጀቱን ቀሲስ ፈንታ ገልጸዋል። በዚህም በኢትዮጵያ ያሉ አንባቢያንን ብቻ ሳይሆን፣ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ፍላጎት ያላቸውን የዓለም ሕዝቦች ለማድረስ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
‎
‎በመጨረሻም የቅዱስ ላሊበላ ታሪክን ማወቅ የአንድን ከተማ ታሪክ ከመረዳት በላይ ለኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ኩራትን ለማጠናከርና ቅርሶችን ለመጠበቅ ያለውን ጠቀሜታ አጉልተዋል። በተለይ ወጣቱ ትውልድ ስለ ቅርሶቹ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ፣ የአገሩን ታሪክ እንዲያውቅና ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያስተላልፍ ጥሪ አቅርበዋል።
‎
‎መጽሐፉን ለማግኘት፦ "A Sacred Rock Built by Faith – Amazon" (https://a.co/d/08eeJyZc)
‎
በጌትነት ተመስገን

‎#lalibela #saintlalibela #ethiopia #ethiopianheritage #rockhewnchurches #lalibelahistory #ethiopianorthodox #orthodoxtewahedo #ethiopianculture #religiousheritage #worldheritage #unescoheritage

3 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.