Logo
YenetaTube
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የጥራት ጉድለት በታየባቸው ሰባት የመድኃኒት ምርቶች ላይ ማሳሰቢያ አወጣ

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የጥራት ጉድለት በታየባቸው እና ከገበያ እንዲሰበሰቡ በተወሰነባቸው ሰባት የመድኃኒት አይነቶች ላይ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።

ባለስልጣኑ ይህንን ማስጠንቀቂያ ያወጣው የኬንያ የመድኃኒት ተቆጣጣሪ አካል በሀገሪቱ በገበያ ላይ በተገኙ የተወሰኑ ምርቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን መነሻ በማድረግ ነው።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመድኃኒት ጥራት እና ደህንነት ክትትል ክፍል አማካሪ ዶ/ር ኤልሳቤት ወልደማርያም እንደተናገሩት ኢትዮጵያ እና ኬንያ ሰፊ ድንበር የሚጋሩ በመሆናቸው እነዚህ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ዕድል አላቸው።

በተለያዩ የጥራት እና የደህንነት ጉድለቶች ምክንያት ከገበያ እንዲሰበሰቡ ከተደረጉት ሰባት የመድኃኒት አይነቶች መካከል በህንድ የተለያዩ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች የተመረቱት
👉ፍላዛርት ሽሮፕ
👉ሄፓካል 25000
👉ቱናክላቭ እና ክላክሲ 1.2 ግራም የተባሉ የመድኃኒት አይነቶች ይገኙበታል።

በተጨማሪም በቻይና ኩባንያ የተመረተው ሜታሚድ መርፌ እና በኬንያ አምራች የተመረተው ክሎክሳም ሽሮፕም ከተሰበሰቡት የመድኃኒት አይነቶች ውስጥ እንደሚገኙበት ተገልጿል።

በዚህም የክልል ተቆጣጣሪ አካላት የእነዚህን ምርቶች ስርጭት እና አጠቃቀም በቅርበት እንዲከታተሉ ያሳሰበው ባለስልጣኑ ህብረተሰቡም ምርቶቹ በእጁ የሚገኙ ከሆነ እንዳይጠቀምባቸው ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

በፋሲል አረጋይ

3 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.