Logo
ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal
በጋና የመገበያያ ገንዘብን ለጌጣጌጥ እና ለኬክ ማስጌጫነት የተጠቀሙ ሰባት ሴቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ

​የጋና ማዕከላዊ ባንክ አገራዊ የመገበያያ ገንዘብን  ለተገቢው አገልግሎት ብቻ ማዋል እንደሚገባ እና በገንዘብ ማስጌጥ ህገ-ወጥ መሆኑን ቀደም ብሎ ማሳሰቡ ይታወሳል።

​የጋና ማዕከላዊ ባንክ ከጋና ፖሊስ አገልግሎት ጋር በመተባበር ባካሄደው ዘመቻ በዋና ከተማዋ አክራ የሀገሪቱን የመገበያያ ገንዘብ  ለጌጣጌጥ፣ ለአበባ እቅፍ እና ለኬክ ማስጌጫነት በመጠቀም ሲሸጡ የነበሩ ሰባት ሴቶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

​እርምጃው የተወሰደው የሀገሪቱን ህጋዊ የመገበያያ ገንዘብ አግባብ ባልሆነ መልኩ የመጠቀም እና የመንከባከብ ልማድን ለመግታት በተደረገ አገር አቀፍ ቁጥጥር መሆኑ ተገልጿል።

​የጋና ማዕከላዊ ባንክ ባለፈው ወር ባወጣው መግለጫ የሴዲ ኖቶችን ለጌጣጌጥም ሆነ ለተለያዩ የአበባ እቅፎች መስሪያነት መጠቀም በህግ የተከለከለ መሆኑን አስጠንቅቆ ነበር።

​ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች ላይ ገንዘብን መበተን፣ ኖቶችን መበጠስ፣ በላያቸው ላይ መጻፍ ወይም የባንክ ኖቶችን ማበላሸት ፈጽሞ የተከለከሉ ድርጊቶች እንደሆኑ ባንኩ አሳስቧል።

​በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰባቱ ተጠርጣሪዎች በጋና ህግ መሰረት ክስ የሚመሰረትባቸው ሲሆን፣ የገንዘብ መቀጮ ወይም የእስራት ቅጣት ሊጠብቃቸው እንደሚችል ተጠቅሷል።

​ባንኩ አክሎ እንደገለጸው ሴዲ የሀገሪቱ ህጋዊ የመገበያያ ገንዘብ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ተገቢውን ክብር እና እንክብካቤ ሊያደርግለት እንደሚገባ አሳስቧል።

ሰላማዊ ነጋሲ
#ዳጉ_ጆርናል
20 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.