Logo
AHADU RADIO FM 94.3
በአሽከርካሪዎች እና አሠሪዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያግዝ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

በአሽከርካሪዎች እና አሠሪዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ወደ ሕግ ከመውሰድ ይልቅ በሦስትዮሽ ውይይት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙ ተገለጸ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን እና የትራንስፖርት ሠራተኞች ፌዴሬሽን በጋራ የተፈራረሙት ሲሆን፣ የአሽከርካሪዎችን መብትና ጥቅም በማስከበር አላስፈላጊ ወጪና የጊዜ ብክነትን ለማስቀረት ያለመ እንደሆነ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኔ ዘሩ ለአሐዱ ሬድዮ እንዳስታወቁት፣ ስምምነቱ የጡረታ አበልን፣ የሥራ ውልን እና ሕጋዊ ማዕቀፎችን በማጠናከር አስተማማኝ የሥራ ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ ነው።

አሽከርካሪዎች የትራንስፖርት ዘርፉ ዋና አንቀሳቃሽ በመሆናቸው የመብት እና ጥቅም ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ማግኘት እንዳለባቸው አቶ ብርሃኔ ገልጸዋል።

የአሽከርካሪዎች መብት እና የሥራ ዋስትና ካልተረጋገጠ የትራንስፖርት ዘርፉም ሆነ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሊጎዳ እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፣ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሥራ ዋስትናቸውን የሚያሻሽሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ተብሏል።

በደረጄ መንግስቱ

#አሐዱ_ሬዲዮ_94 .3
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.