Logo
FastMereja
“ብርሃናተ ዓለም” ተብለው ይጠራሉ

በአባቱ የሮቤል፣ በእናቱ የስምዖን ነገድ ሲኾን፣ የተወለደውም በገሊላ አውራጃ በቤተ ሳይዳ ነው፡፡ ወላጆቹ ያወጡለት ስም ስምዖን ነበር፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ጴጥሮስ ብሎ ጠርቶታል፡፡ ትርጕሙም በግሪክ ቋንቋ ዓለት መሠረት ማለት ነው፡፡ በዓሣ አጥማጅነት ሲተዳደረው የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ሰዎችን በወንጌል መረብ እያጠመደ ወደ ክርስትና ሕይወት ይመልስ ዘንድ ጌታችን ለሐዋርያነት ጠርቶታል፡፡ በመንፈሳዊ ቅንዓቱና ለጌታችን በነበረው ፍቅር የሐዋርያት አለቃ ሆኖ ተሹሟል፡፡ ለአገልግሎት ከተጠራበት ጊዜ ጀምሮም በእስያ፣ በሮም፣ በሰማርያ፣ በልዳ፣ በኢዮጴ፣ በአንጾኪያ፣ በገላትያና በሌሎችም አገሮች እየተዘዋወረ ወንጌልን ሰብኳል፤ ብዙ መከራም ተቀብሏል፡፡ በክርስቶስ ኀይል አጋዥነት ብዙ ድንቆችንና ተአምራትን አድርጓል፡፡

በሐዋርያት 5÷15 እንደተጻፈው ከተሰጠው ጸጋ ብዛት የተነሣ በጥላው ሕሙማን ይፈወሱ ነበር፡፡ በቃል ካስተማረው ትምህርት በተጨማሪ በመጽሐፍ ቅዱስ በስሙ የተመዘገቡትን 1ኛ እና 2ኛ መልእክቶቹን ጽፏል፡፡ በምድራዊ አገልግሎቱ ማብቂያ ላይ የክርስቲያኖች ጠላት የነበረው የሮም ንጉሥ በጦርነት ድል በማድረጉ ተደስቶ ጣዖታቱንም ለማክበር ሲል በቅዱስ ጴጥሮስና በሌሎችም ክርስቲያኖች ላይ የሞት ፍርድ ዐወጀ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በሮም ሲያስተምር ቆይቶ መኳንንቱ እንዳይገድሉት ትጥቁን ለውጦ ሲወጣ ጌታችን መስቀል ተሸክሞ ተገለጸለት፡፡ በዚህ ጊዜ “አቤቱ ጌታ ሆይ ወዴት ትሔዳለህ?” ሲል ቢጠይቀው ጌታችንም “አንተ መሰቀልን ስትፈራ ዳግም ልሰቀል እየሔድኩ ነው” ሲል መለሰለት፡፡ ያን ጊዜ ወደ ሮም ተመልሶ ስብከቱን ቀጠለ፡፡ በሕጋቸው መሠረትም ዜግነቱ ሮማዊ አልነበረምና በግርፋት፣ በእስራትና በሞት እንዲቀጣ ተፈረደበት፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ለአገልግሎት ከመጠራቱ በፊት ሳውል ይባል ነበር፡፡ ከኦሪቱ ምሁር ከገማልያል ሕገ ኦሪትንና መጻሕፍተ ነቢያትን ተምሯል፡፡ ለሕገ ኦሪት ከመቆርቆሩ የተነሣም የክርስቶስ ተከታዮችን ሁሉ ያሳድድ ነበር፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተደብድቦ ሰማዕትነት ሲቀበል ቅዱስ ጳውሎስ የገዳዮቹ ልብስ ጠባቂ ነበር፡፡ በሐዋርያት 9÷1-31 እንደተገለጸው ወደ ደማስቆ ሲሔድ ከመንገድ ላይ ለሐዋርያነት ተጠርቷል፡፡ ከዚህ ጀምሮም በመላው ዓለም እየተዘዋወረ ጣዖት አምላኪ፣ ሕመምተኛ፣ ችግረኛ፣ አረማዊና አይሁዳዊ እየመሰለ ብዙዎችን አስተምሮ ለእግዚአብሔር መንግሥት አዘጋጅቷል፡፡ በልብሱ ቅዳጅም ሕሙማን ይፈወሱ ነበር፡፡ ከአይሁድና ከአረማውያን ዘንድ ብዙ መከራና ስቃይ ደርሶበታል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም በስሙ የተመዘገቡ 14 መልእክታት አሉት፡፡

አገልግሎቱን ሊፈጽም ሲልም የሮም ንጉሥ ኔሮን ቄሣር የክርስቲያኖች ቍጥር እየጨመረ የመጣው በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት መኾኑን የቤተ መንግሥቱ ሰዎች ሳይቀር በቅዱስ ጳውሎስ በመማረካቸው ተቈጥቶ ይሙት በቃ ፈረደበት፡፡ ወታደሮች ሊገድሉት ሲወስዱትም ከንጉሥ ኔሮን ወገን የሆነች ብላቴና መጐናጸፊያ “ዛሬ እመልስልሻለሁ” ብሎ ተቀበላትና ፊቱን በብላቴናዋ መጐናጸፊያ ተሸፍኖ አንገቱን በሰይፍ ተቀልቶ አገልግሎቱን በሰማዕትነት ፈጽሟል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ራሱን ከአንገቱ ጋር ቢያደርጉት እንደ ቀድሞው ደኅና ኾኖላቸው በክብር ገንዘው ቀብረውታል፡፡ ሰያፊው ተግባሩን መፈጸሙን ለመናገር ወደ ንጉሡ ሲመለስም ያቺ መጐናጸፊያዋን የሰጠችው ብላቴና “እነሆ ጴጥሮስና ጳውሎስ በእኔ በኩል አልፈው ሔዱ፡፡ የመንግሥት ልብስ ለብሰው፣ በራሳቸውም በዕንቍ ያጌጡ አክሊላትን አድርገዋል፡፡ ይህችን መጐናጸፊያዬንም ሰጡኝ” ብላ ከእርሱ ጋር ለነበሩትም አሳየቻቸው፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡ ቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ጨለማውን ዓለም በማድመቃቸው “ብርሃናተ ዓለም” ተብለው ይጠራሉ፡፡ በረከታቸውን ያመኑ ገዳማውያንም ስለክርስቶስ ፍቅር ዓለምን ትተው ይከተሏቸዋል፡፡ ገዳማቸውን እንደግፍ በዓታቸውን እናጽና፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.