Logo
Getu Temesgen
ህሩይ የፋሽንና የውበት ማሰልጠኛ ት/ቤት 140 ተማሪዎችን አስመረቀ
#ethiopia | በእንጅባራ ከተማ የሚገኘው ህሩይ የፋሽንና የውበት ማሰልጠኛ ት/ቤት በ5ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 140 ተማሪዎች በድምቀት አስመርቋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ም/መምሪያ ኃላፊ ስንታየሁ መንግስቱ፣ ተቋሙ በከተማዋ የሚገኙ ወጣቶች በጋርመንት ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

የፋሽንና የጋርመንት ዘርፍ በቀጣይነት አዳዲስ እሳቤዎችንና የላቀ ክህሎትን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ተመራቂዎቹ በሰለጠኑበት ሙያ ብቻ ሳይወሰኑ በቀጣይም እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ዘርፉ የፈጠራ ክህሎትን የሚጠይቅ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፣ ወጣቶች በጋርመንት ቴክኖሎጂ በስፋት በመሰማራት የሥራ ዕድል ፈጥረው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። በተጨማሪም ሥራቸውን የማኅበረሰቡን ወግና ባህል በጠበቀ መልኩ እንዲያከናውኑ ለተመራቂዎቹ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።

የህሩይ የፋሽንና የውበት ማሰልጠኛ ት/ቤት መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ህሩይ አምደወርቅ በበኩሉ፣ ት/ቤቱ በፋሽንና በውበት ዘርፍ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ያለ ተቋም መሆኑን ተናግሯል።

በተለይም እየተነቃቃ የመጣውን የባህል አልባሳት በማዘመንና ከዘመኑ ፋሽን ጋር በማጣጣም ወጣቶችን የሙያ ባለቤት ማድረግ የት/ቤቱ ዋና ዓላማ መሆኑን ገልጿል።

ህሩይ የፋሽንና የውበት ማሰልጠኛ ት/ቤት በ5ኛ ዙር የገበያውን ፍላጎት ያሟላሉ ብሎ ያመናቸውን 140 ተማሪዎች አሰልጥኖ ማስመረቁንም ገልጿል።

ወጣት ህሩይ እንደገለጸው፣ የፋሽንና የጋርመንት ዘርፍ በአነስተኛ ወጪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሰፊ አቅም ያለው ዘርፍ ነው። ይህም ሀገሪቱ የያዘችውን የዕድገት ጎዳና ለማፋጠን ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቁሟል።

ዘርፉ አሁንም በሀገር ውስጥ በሙሉ አቅሙ ያልተለማ መሆኑን የገለጸው ወጣት ህሩይ፣ ከውጭ የሚገቡ አልባሳትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተደረገ ላለው ጥረት ተቋሙ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመላክቷል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የ5ኛ ዙር ሰልጣኝ ተመራቂዎች በሰሯቸው የሙያ ሥራዎች ተወዳድረው ለውጤታማ ተማሪዎች ሜዳሊያዎችና ሽልማቶች ተበርክተዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል 13 ዓመቷ ታዳጊ ፀደኒያ ታደለ ከመደበኛ ትምህርቷ ጎን ለጎን የሙያ ባለቤት ለመሆን በማሰብ ስልጠናውን በስኬት አጠናቃ ተመርቃለች።

ታዳጊዋ በምረቃው ዕለት በራሷ የሰራችውን የሙያ ሥራ ይዛ በውድድሩ ተሳትፋ አንደኛ ደረጃን በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።

ይህም የወጣቶችና የታዳጊዎች የሙያ ትምህርት ከመደበኛ ትምህርት ጋር ተጣምሮ ለቀጣይ ሕይወታቸው ጠቃሚ ክህሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ያሳያል።

3 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.