Logo
FastMereja
በሲዳማ ክልል ጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ግብዓት ጥራት ቁጥጥር ሥርዓትን ዲጂታል በማድረግ የአገልግሎት ፍጥነትና ጥራትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

በሲዳማ ክልል የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ግብዓት ጥራት ቁጥጥር ሥርዓትን ዲጂታል በማድረግ የአገልግሎት ፍጥነትና ጥራትን ለማሳደግ፣ የወረቀት አጠቃቀምንና የተገልጋዮችን መንከራተት ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው የሲዳማ ክልል ጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ግብዓት ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የጤና ሚኒስቴርና JSI Research & Training Institute, Inc. በጋራ ባዘጋጁት ሁለተኛ ዙር ሥልጠና ላይ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ግብአት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቡሪሶ ቡላሾ ባስተላለፉት መልዕክት ፣ የዘርፉን ስራዎች የቁጥጥር ሥርዓቱን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር የአገልግሎት ጥራትን ማሻሻልና የተገልጋዮችን እንግልት መቀነስ እየተቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለሥልጣኑ መ/ቤት የጤና ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ፣ የጤና ባለሙያዎች ፈቃድ እድሳትና የተቋማት ቦታ ለውጥ ሂደቶችን ዲጂታል በማድረግ የወረቀት አሠራርንና ከተቋም ወደ ተቋም መመላለስን ለመቀነስ እየሰራ ያለው ስራ ውጤታማና አበረታች መሆኑን አመልክተዋል።

አቶ ቡሪሶ አክለው እንዳሉት፣ አገልግሎቶችን ዲጅታላይዝ ማድረግ የቁጥጥር ሥራን በመረጃ ማስደገፍ የቁጥጥር ሂደቱ ወቅታዊና ቀልጣፋ እንዲሆን ያግዛል ብለዋል ። በቀጣይም የቁጥጥር ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ ይበልጥ ለማጠናከር የተጀመሩ ሰፊ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለዘርፉ ባለሙያዎች እየተሰጠ ያለው ስልጠና ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጤና ሚኒስቴር የጤናና ጤና ነክ ተቋማትና ባለሙያዎች ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንዳልካቸው ፀዳል እንደገለጹት፣ ጥራቱን የጠበቀና ውጤታማ የጤና አገልግሎትን ለማረጋገጥ በታቀደው ሥራና በተግባራዊ አፈጻጸም መካከል ያለውን ክፍተት ማጥበብ ያስፈልጋል።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ወደ ቁጥጥር ሥርዓቱ ማስገባት የቁጥጥር ሂደቶችን ከማዘመን ባለፈ ተቋማዊ ለውጥን ለማፋጠንና አገልግሎቱን ለማሳለጥ የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።

3 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.