Logo
ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal
አዲስ ሕይወት ጄኔራል ሆስፒታል ለላንቃ እና ከንፈር መሰንጠቅ የሚሰጠውን ነፃ ህክምና ወደ ሙሉ ማዕቀፍ አሳደገ

አዲስ ሕይወት ጄኔራል ሆስፒታል ከዓለም አቀፉ 'ስማይል ትሬን' እና 'ሪስቶሪንግ ስማይል' ጋር በመተባበር የላንቃ እና የከንፈር መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው ህፃናት ሲሰጥ የነበረውን ነፃ የቀዶ ጥገና አገልግሎት በማስፋት ሙሉ የሕክምና ማዕቀፍ መስጠት መጀመሩን አስታውቋል።

የዓለም የፈገግታ ቀንን አስመልክቶ ማዕከሉ ከቀዶ ሕክምናው በተጨማሪ የስነ-ምግብ፣ የአነጋገር ማስተካከያ፣ የጥርስ እና የአፍ ንፅህና እንዲሁም የስነ-ልቦና ድጋፍን ያካተተ ነፃ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጿል ።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሚካኤል ተስፋዬ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከ130 በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የቀዶ ሕክምና እንዲሁም ለሌሎች በርካታ ህፃናት ተያያዥ የቴራፒ ህክምናዎችን ለመስጠት ታቅዷል።

ሪስቶሪንግ ስማይል' በበኩሉ በዘንድሮው ዓመት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ 175 ህፃናትን ለይቶ ወደ ህክምና ለማምጣት እየሰራ መሆኑን የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም መኮንን ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል።

የታካሚዎች እና የአጋዥ ቤተሰቦቻቸው ትራንስፖርት፣ ምግብ፣ ማረፊያ እና ሙሉ የሕክምና ወጪ በዓለም አቀፉ 'ስማይል ትሬን' ድርጅት ሙሉ በሙሉ የሚሸፈን መሆኑን የተናገሩት አቶ ቢኒያም፣ የላንቃ እና ከንፈር መሰንጠቅ ሙሉ በሙሉ በህክምና የሚስተካከል እንጂ እርግማን ባለመሆኑ፤ ህብረተሰቡ ችግሩ ያለባቸውን ህፃናት በመደበቅ ፈንታ ወደ ጤና ተቋማት በመውሰድ የነፃ ህክምናው ተጠቃሚ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በሚኪያስ ፀሐዬ

#ዳጉ_ጆርናል
5 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.