Logo
ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal
በአሜሪካን ሐገር የ3 ዓመት ህፃን ልጅ ጥይት የተሞላበት ሽጉጥ የህፃናት ማቆያ ስፍራ ውስጥ ይዞ ተገኘ

በአሜሪካ ሚቺጋን ግዛት፣ ካንተን ታውንሺፕ በሚገኝ የህፃናት ማቆያ ውስጥ አንድ የሶስት ዓመት ህጻን ጥይት የተሞላበት ሽጉጥ በጀርባ ቦርሳው ይዞ ወደ ህጻናት ማቆያ መግባቱ የተሰማ ሲሆን፣ ድርጊቱን ተከትሎ የህጻኑ እናት በቁጥጥር ስር መዋሏን የጸጥታ አካላት አስታውቀዋል።

ይህ አስደንጋጭ ክስተት የተፈጠረው ‘ቺልድረንስ ዎርልድ’ በተሰኘው የህጻናት ማቆያ እና ማስተማሪያ ማዕከል ውስጥ ነው። የካንተን ፖሊስ አዛዥ ጆሴፍ ቢያሊ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ህጻኑ ሽጉጡን ከቦርሳው አውጥቶ ሲጫወትበት በክፍሉ ውስጥ የነበሩት መምህርት በአስቸኳይ ጣልቃ በመግባት መሳሪያውን በሰላም መቀማትና ማስጣል ችለዋል።

በዚህም ምክንያት በአካባቢው በነበሩት ህጻናትም ሆነ ሰራተኞች ላይ ምንም አይነት የአካል ጉዳት ሳይደርስ አደጋውን መከላከል ተችሏል።ፖሊስ እንዳስታወቀው ከሆነ ህጻኑ ይዞት የገባው መሳሪያ ‘ግሎክ’ የተሰኘ ሽጉጥ ሲሆን፣ የመሳሪያው ባለቤት ደግሞ የህጻኑ እናት መሆኗ ታውቋል። ሙያዋ ነርስ የሆነችው ይህቺው እናት በቸልተኝነት እና የጦር መሳሪያን በአግባቡ ባለመጠበቅ ወንጀል ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር ውላለች።

የሚገርመው ነገር ደግሞ የህፃኑ ልጅ አባት በከተማው ውስጥ ህግ የሚያስከብር የከተማው ፖሊስ አባል መሆኑ ድርጊቱን ይባልጥ አነጋጋሪ አድርጎታል። ልጁ ግን ትምህርት ቤቱ ውስጥ ይዞት የተገኘው የፖሊስ አባቱን የመስሪያ ቤት ሽጉጥ እንዳልሆነ ተገልጿል።

መምህሯ መጀመሪያ ላይ ልጁ ሽጉጡን ከቦርሳው አውጥቶ ወደ ሌሎች ህፃናት ሽጉጡን ሲያነጣጥር ስትመለከት የአሻንጉሊት አርቴፊሻል ሽጉጥ መስሏት ነበር፣ በኋላ ግን ሽጉጡ ከፕላስቲክ ያልተሰራ እና የእውነተኛ ሽጉጥ መሆኑን ስታቅ፣ ከጀርባው ሄደ ቀስ ብላ ሽጉጡን ከህፃኑ ልትቀበለው ችላለች።የማዕከሉ መምህራን ላሳዩት ፈጣን እና ብልህ እርምጃ የፖሊስ አዛዡ ከፍተኛ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ ጉዳዩ በዋይን ካውንቲ ዓቃቤ ህግ በኩል ተመርምሮ ክስ የመመስረት ሂደት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ክስተቱ የወላጆችን የጦር መሳሪያ አያያዝ ጥንቃቄ በጥብቅ የፈተነ መሆኑን የመገናኛ ብዙኃን በስፋት እየዘገቡት ይገኛሉ።

#ዳጉ_ጆርናል
7 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.