Logo
FastMereja
ጆይ ኦቲዝም ማዕከል እያስገነባ የሚገኘዉን ህንፃ ለማጠናቀቅና ለብዙዎች ተስፋ ለመሆን የድጋፍ ጥሪ አቀረበ!
#fastmereja :-የኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል በኦቲስቲክ ህፃናት ድጋፍና ስልጠና ላይ የተጋረጡ የመሰረተ ልማትና የቦታ ጥበት ችግሮችን ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት የሚያስችለውን አዲስ ዘመናዊ ህንፃ የመሰረትና የአፅም (G+6) ግንባታ ሙሉ በሙሉ አጠናቆ በፊኒሺንግ (የማጠናቀቂያ) ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ በዛሬዉ እለት አስታወቀ።

የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ እሌኒ ዳምጠው እንደገለጹት፣ ከመንግስት በተሰጠ 4,804 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ4 ዓመታት ውስጥ እየተገነባ የሚገኘዉ ይህ ህንፃ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ማዕከሉ በቀጣይ በስፋትና በተሻለ ጥራት ለኦቲስቲክ ህፃናት፣ ወጣቶችና ቤተሰቦቻቸው የሕክምና፣ የትምህርት፣ የሙያ ስልጠናና የስነ-ልቦና ድጋፍ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችለዉ ገልፀዋል።

ከተመሰረተ ከ24 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ይህ የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ ባለፉት ዓመታት ከ2,500 በላይ ለሚሆኑ የኦቲዝም ተጽዕኖ ያለባቸው ህፃናትና ወላጆቻቸው ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም 120 ልጆችን በቀጥታ የሚያስተናግድ ሲሆን፣ 57 ሰራተኞችን በመያዝ ቤት ለቤት የድጋፍ ስራዎችንና የማህበረሰብ ግንዛቤ የመፍጠር እንቅስቃሴዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ነዉ የተገለፀዉ።

የህንፃውን የማጠናቀቂያ ስራዎች በፍጥነት ለማጠናቀቅ በተደረጉ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች፣ የማዕከሉ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር አቶ ዳንኤል እቁባይ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው የተሰበሰበውን 1.5 ሚሊዮን ብር እና የራሳቸውን 1.5 ሚሊዮን ብር በማከል በአጠቃላይ 3 ሚሊዮን ብር ለህንፃው ግንባታ ገቢ ማድረጋቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ለህንፃው ሊፍት ገጠማ የሚሆን 8 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ አዲስ የቻሌንጅ እንቅስቃሴ ከማዕከሉ ጋር በመተባበር በይፋ መጀመሩን የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ጠቁመዋል።

እንዲሁም የማዕከሉ አመራሮች ህብረተሰቡና አቅም ያላቸው ወገኖች በገንዘብም ሆነ በእቃ ድጋፍ በማድረግ የህንፃውን ግንባታ ለማጠናቀቅና ለብዙ ልጆችና ቤተሰቦች ተስፋ ለመሆን ከጎናቸው እንዲቆሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ኒያ ፋውንዴሽን( ጆይ ኦቲዝም ማዕከል) በወ/ሮ ዘሚ የኑስ ተመስርቶ ከፖለቲካና ከሃይማኖት ነፃ በሆነ መልኩ በኢትዮጵያ በኦቲስቲክ ህፃናት፣ ወጣቶችና ቤተሰቦቻቸው ድጋፍ፣ ስልጠና፣ ህክምና እና ክብካቤ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው።

15 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.